1ሳምሶን ወደ ጋዛ ሄደና በዚያ ዝሙት አዳሪ ሴት አየ፣ ከእርስዋም ጋር ወደ አልጋ ሄደ፡፡
2የጋዛ ሰዎችም “ሳምሶን ወደዚህ መጥቶአል” የሚል ወሬ ሰሙ፡፡ የጋዛ ሰዎች ስፍራውን ከበቡትና ሌሊቱን ሁሉ ተደብቀው በከተማይቱ በር ጠበቁት፡፡ ሌሊቱን ሁሉ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አላደረጉም፡፡ እንዲህ ብለዋልና፣ “እስኪነጋ ድረስ እንጠብቀው፣ ከዚያም እንገድለዋለን፡፡”
3ሳምሶንም እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በአልጋ ላይ ተኛ፡፡ እኩለ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ተነሳና የከተማይቱን በር መዝጊያና ሁለቱን መቃኖች ያዘ፡፡ እነርሱንም ከመወርወሪያው ጋር ከመሬት ነቀላቸው፣ በትከሻውም ላይ አደረጋቸው፣ በኬብሮንም ፊት ለፊት ወዳለው ኮረብታ ራስ ላይ ተሸክሞት ወጣ፡፡
4ከዚህ በኋላ ሳምሶን በሶሬቅ ሸለቆ የምትኖር አንዲት ሴት ወደደ፡፡ ስምዋም ደሊላ ይባል ነበር፡፡
5የፍልስጥኤማውያንም አለቆች ወደ እርስዋ መጡና እንዲህ አሏት፣ “እርሱን ለማዋረድ እናስረው ዘንድ በእርሱ ያለው ታላቅ ኃይል የት እንደሆነና በምን መንገድ እርሱን ማሸነፍ እንደምንችል እንዲያሳይሽ ሳምሶንን አባብዪው፡፡ ይህንን አድርጊልን፣ እኛም እያንዳንዳችን 1, 100 ብር እንሰጥሻለን፡፡
6ደሊላም ለሳምሶን እንዲህ አለችው፣ “እባክህ፣ እንዲህ በጣም ብርቱ የሆንከው እንዴት እንደሆነ ንገረኝ፣ በቁጥጥር ስር መዋል እንድትችል ሰው ሊያስርህ የሚችለው እንዴት ነው?
7ሳምሶንም እንዲህ አላት፣ “ባልደረቁ ሰባት እርጥብ ጠፍሮች ቢያስሩኝ፣ እደክማለሁ፣ እንደ ማንኛውም ሰውም እሆናለሁ፡፡”
8የፍልስጥኤማውያን አለቆችም ያልደረቁ ሰባት እርጥብ ጠፍሮች አመጡላት፣ እርስዋም ሳምሶንን በእነርሱ አሰረችው፡፡
9በዚህን ጊዜ በጓዳዋ ውስጥ ሰዎች በምስጢር ተደብቀው ይጠብቁ ነበር፡፡ እርስዋም፣ “ሳምሶን፣ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው፡፡ ነገር ግን የተልባ እግር ፈትል እሳት በነካው ጊዜ እንደሚበጣጠስ ጠፍሩን በጣጠሰው፡፡ እነርሱም የብርታቱ ምስጢር ምን እንደሆነ አላወቁም፡፡
10ከዚያም ደሊላ ሳምሶንን እንዲህ አለችው፣ “አንተ እኔን እንዴት እንዳታለልኸኝ ግልጽ ሆኗል፣ ሐሰትንም ነገርኸኝ፡፡ እባክህ፣ እንዴት እንደምትታሰር ንገረኝ፡፡”
11እርሱም እንዲህ አላት፣ “ለሥራ ጥቅም ላይ ፈጽሞ ባልዋሉ በአዲስ ገመዶች ቢያስሩኝ፣ እደክማለሁ፣ እንደ ማንኛውም ሰው እሆናለሁ፡፡”
12ስለዚህ ደሊላ አዲስ ገመዶች ወሰደችና በእነርሱ አሰረችው፣ እንዲህም አለችው፣ “ሳምሶን፣ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ፡፡” ተደብቀው ሲጠብቁ የነበሩት ሰዎች በጓዳዋ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሳምሶን ገመዶቹን እንደ ፈትል ክር ከክንዶቹ በጣጠሰው፡፡
13ደሊላም ሳምሶንን እንዲህ አለችው፣ “እስከ አሁን ድረስ አታልለኸኛልና የነገርኸኝም ውሸት ነው፡፡ አንተን ማሰር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ንገረኝ፡፡” ሳምሶንም እንዲህ አላት፣ “የራሴን ጠጕር ሰባቱን ጕንጕን ከድር ጋር ጎንጉነሽ በችካል ብትቸክዪው፣ እንደ ሌላ ሰው እሆናለሁ፡፡”
14እርሱም በተኛ ጊዜ፣ ደሊላ የራሱን ጠጕር ሰባቱን ጕንጕን ከድሩ ጋር ጐነጐነችው፣ በችካልም ቸከለችውና፣ እንዲህ አለችው፣ “ሳምሶን፣ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ!” እርሱም ከእንቅልፉ ነቃና ችካሉን ከነቆንዳላውና ከነድሩ ነቀለው፡፡
15እርስዋም እንዲህ አለችው፣ “ምስጢርህን ለእኔ ሳትነግረኝ ‘እወድሻለሁ’ ልትለኝ እንዴት ትችላለህ? ሦስት ጊዜ ቀለድህብኝ፣ እንዲህ ዓይነቱን ታላቅ ኃይል እንዴት ሊኖርህ እንደቻለ አልነገርኸኝም፡፡”
16ሞት እስኪመኝ ድረስ ዕለት ዕለት በቃሎችዋ እጅግ በጣም ጨቀጨቀችው፣ ከመጠን በላይም ጫና አደረገችበት፡፡
17ስለዚህ ሳምሶን ሁሉንም ነገር ነገራትና እንዲህ አላት፣ “ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ ለእግዚአብሔር ናዝራዊ ሆኜ ስለተለየሁ በራሴ ላይ ምላጭ ደርሶና ጸጉሬን ተላጭቼ አላውቅም፡፡ የራሴን ጸጕር ብላጭ ኃይሌ ከእኔ ይሄዳል፣ እደክማለሁም እንደ ማንኛውም ሰው እሆናለሁ፡፡”
18ደሊላም ስለ ሁሉ ነገር እውነቱን እንደነገራት ባየች ጊዜ፣ ሰዎች ላከችና የፍልስጥኤማውያንን አለቆች ጠራች፣ እንዲህም አለቻቸው፣ “ሁሉንም ነገር ነግሮኛልና እንደገና ኑ፡፡” የዚያን ጊዜ የፍልስጥኤማውያን አለቆች ብሩን በእጃቸው ይዘው ወደ እርስዋ ሄዱ፡፡
19እርስዋም በጭኗ ላይ እንዲተኛ አደረገችው፡፡ ሰባቱን የራሱን ጕንጕን እንዲላጨው አንድ ሰው ጠራች፣ ኃይሉ ስለተለየው እርስዋ በቁጥጥሯ ስር ልታደርገው ጀመረች፡፡
20እርስዋም፣ “ሳምሶን፣ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ!” አለችው፡፡ እርሱም ከእንቅልፉ ነቅቶ እንዲህ አለ፣ “እንደ ሌላው ጊዜ እወጣለሁ፣ ራሴንም ነጻ አወጣለሁ፡፡” ነገር ግን እግዚአብሔር እንደ ተወው አላወቀም፡፡
21ፍልስጥኤማውያንም ያዙትና ዓይኖቹን አወጡት፡፡ ወደ ጋዛም ወሰዱትና በናስ ሰንሰለት አሰሩት፡፡ በእስር ቤትም ውስጥ ሆኖ እህል ይፈጭ ነበር፡፡
22ነገር ግን ከተላጨ በኋላ የራሱ ጠጕር እንደገና ያድግ ጀመር፡፡
23የፍልስጥኤማውያንም አለቆች ለአምላካቸው ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፣ ደስም ይላቸው ዘንድ በአንድ ላይ ተሰበሰቡ፡፡ እነርሱ “አምላካችን ጠላታችንን ሳምሶንን አሸንፏል፣ በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶናል” ብለዋልና፡፡
24ሕዝቡም እርሱን ባዩት ጊዜ አምላካቸውን አመሰገኑ፣ እንዲህ ብለዋልና፣ “አገራችንን ያጠፋውን፣ ከእኛም ብዙ ሰው የገደለውን ጠላታችንን አምላካችን አሸነፈው፣ በእጃችንም አሳልፎ ሰጠው፡፡”
25እጅግ ደስ ባላቸው ጊዜ፣ እንዲህ አሉ፣ “እንዲያስቀን ሳምሶንን ጥሩት፡፡” ሳምሶንን ከእስር ቤት ጠሩትና እንዲስቁ አደረጋቸው፡፡ በምሰሶና በምሰሶ መካከል እንዲቆም አደረጉት፡፡
26ሳምሶንም እጁን የያዘውን ልጅ፣ “እደገፍባቸው ዘንድ ሕንጻውን የደገፉትን ምሰሶዎች እንድነካቸው አስጠጋኝ” አለው፡፡
27በዚያን ጊዜ ቤቱ በወንዶችና በሴቶች ተሞልቶ ነበር፡፡ የፍልስጥኤም አለቆች ሁሉ በዚያ ነበሩ፡፡ ሳምሶን እነርሱን ሲያዝናናቸው ይመለከቱ የነበሩ ሦስት ሺህ የሚያህሉ ወንዶችና ሴቶች በጣራው ላይ ነበሩ፡፡
28ሳምሶንም ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጮኸ፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ እንደገና አስበኝ! አምላኬ ሆይ፣ ሁለት ዓይኖቼን ስላወጡ ፍልስጥኤማውያንን አሁን በአንድ ምት እንድበቀል፣ እባክህ፣ ይህን አንድ ጊዜ ብቻ አበርታኝ፡፡”
29ሳምሶንም ሕንጻው ተደግፎባቸው የነበሩትን ሁለቱን መካከለኞች ምሰሶዎች ጠምጥሞ ያዘ፣ አንዱን ምሰሶ በቀኝ እጁ ሌላውን ደግሞ በግራ እጁ ይዞ በእነርሱ ላይ ተደገፈ፡፡
30ሳምሶንም እንዲህ አለ፣ “ከፍልስጥኤማውያን ጋር ልሙት!” በሙሉ ኃይሉ ገፋው፣ ሕንጻውም በውስጡ በነበሩት አለቆችና በሕዝቡም ሁሉ ላይ ወደቀ፡፡ ስለዚህ እርሱ በሞተ ጊዜ የገደላቸው ሰዎች በሕይወት ሳለ ከገደላቸው ይልቅ የበለጡ ነበሩ፡፡
31የዚያን ጊዜ ወንድሞቹና የአባቱ ቤተ ሰቦች በሙሉ ወረዱ፣ እርሱንም ይዘው ወሰዱት፣ መልሰው አመጡትና በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በአባቱ በማኑሄ መቃብር ውስጥ ቀበሩት፡፡ ሳምሶን በእስራኤል ላይ ለሀያ ዓመት ፈረደ፡፡