መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መሳፍንት 15

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከጥቂት ቀናትም በኋላ በስንዴ መከር ጊዜ፣ ሳምሶን የፍየል ጠቦት ይዞ ሚስቱን ሊጠይቅ ሄደ፡፡ ለራሱም እንዲህ አለ፣ “ወደ ሚስቴ ወደ ጫጉላው ቤት ልግባ፡፡” ነገር ግን አባትዋ ወደ ውስጥ እንዳይገባ ከለከለው፡፡
2አባትዋም እንዲህ አለ፣ “እኔ በእርግጠኝነት የጠላሃት መሰለኝ፣ ስለዚህም ለጓደኛህ ሰጠኋት፡፡የእርስዋ ታናሽ እኅት ከርስዋ የበለጠች ቆንጆ ናት፣ አይደለችም እንዴ? በእርስዋ ፋንታ ታናሽዋን ውሰዳት፡፡”
3ሳምሶንም ለእነርሱ እንዲህ አላቸው፣ “ከእንግዲህ ወዲህ በፍልስጥኤማውያን ላይ ጉዳት ባደረስሁባቸው ጊዜ እኔ ንጹሕ ነኝ፡፡”
4ሳምሶንም ሄደና ሦስት መቶ ቀበሮዎች ያዘ፣ ሁለት ሁለቱንም ቀበሮዎች በአንድ ላይ በጅራታቸው አሰራቸው፡፡ ከዚያም ችቦዎችን ወስዶ በእያንዳንዱ ጥንድ በሁለቱም ጅራቶች መካከል አሰራቸው፡፡
5ችቦውንም በእሳት ባቀጣጠለው ጊዜ፣ ቀበሮዎቹን በቆመው በፍልስጥኤማውያን እህል መካከል እንዲሄዱ አደረጋቸው፣ የእህሉን ነዶና በእርሻ ውስጥ የቆመውንም እህል፣ ከወይኑ አትክልት ስፍራና ከወይራውም ተክል ጋር አቃጠሉት፡፡
6ፍልስጥኤማውያንም እንዲህ በማለት ጠየቁ፣ “ይህን ያደረገው ማን ነው?” እነርሱም “ይህን ያደረገው የተምናዊው አማች ሳምሶን ነው፣ ምክንያቱም ተምናዊው የሳምሶንን ሚስት ወስዶ ለጓደኛው ሰጥቶአታልና” አሉ፡፡ ፍልስጥኤማያንም ሄደው እርስዋንና አባትዋን በእሳት አቃጠሉ፡፡
7ሳምሶንም “እናንተ ይህንን ካደረጋችሁ፣ እኔ እበቀላችኋለሁ፣ እኔ የማርፈው ይህን ካደረግሁ በኋላ ነው” አላቸው፡፡
8እርሱም ዳሌአቸውንና ጭናቸውን ቆራረጣቸውና በታላቅ አገዳደል ገደላቸው፡፡ ከዚያም ወርዶ በኤጣም ዓለት ባለው ዋሻ ውስጥ ተቀመጠ፡፡
9የዚያን ጊዜ ፍልስጥኤማውያን ወጡና በይሁዳ ጦርነት ለማካሄድ ተዘጋጁ፣ ሰራዊታቸውንም በሌሒ ውስጥ አሰፈሩ፡፡
10የይሁዳም ሰዎች እንዲህ አሉ፣ “እኛን ለመውጋት የመጣችሁት ለምንድን ነው?” እነርሱም እንዲህ አሉ፣ “የምንወጋችሁ ሳምሶንን ለመያዝ ነው፣ እርሱ በእኛ ላይ እንዳደረገው እኛም በእርሱ ላይ ልናደርግበት ነው፡፡”
11ሦስት ሺህ የይሁዳ ሰዎችም በኤጣም ዓለት ወዳለው ዋሻ ወረዱና፣ ለሳምሶን እንዲህ አሉት፣ “ፍልስጥኤማውያን በእኛ ላይ ገዢዎች እንደሆኑ አታውቅምን? ይህ በእኛ ላይ ያደረግኸው ነገር ምንድን ነው?” ሳምሶንም ለእነርሱ እንዲህ አላቸው፣ “እነርሱ በእኔ ላይ አደረጉብኝ፣ እኔም በእነርሱ ላይ አደረግሁባቸው፡፡”
12እነርሱም ለሳምሶን እንዲህ አሉት፣ “አንተን አስረን ለፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፈን ልንሰጥህ መጥተናል፡፡” ሳምሶንም እንዲህ አላቸው፣ “እናንተ ራሳችሁ እንደማትገድሉኝ ማሉልኝ፡፡”
13እነርሱም እንዲህ አሉት፣ “አንገድልህም፣ በገመድ አስረን ብቻ ለእነርሱ አሳልፈን እንሰጥሃለን፡፡ እንደማንገድልህ ቃል እንገባልሃለን፡፡” ከዚያም በሁለት አዲስ ገመዶች አሰሩትና ከዓለቱ ውስጥ አወጡት፡፡
14ወደ ሌሒ በመጣ ጊዜ፣ ፍልስጥኤማውያን እየጮሁ መጡ፣ አገኙትም፡፡ የዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ በኃይል ወረደበት፡፡ ክንዶቹ የታሰሩበት ገመዶችም በእሳት እንደ ተቃጠለ የተልባ እግር ፈትል ከእጆቹ ላይ ወደቁ፡፡
15ሳምሶንም አዲስ የአህያ መንጋጋ አገኘ፣ እጁንም ዘርግቶ አነሳውና በእርሱ አንድ ሺህ ሰዎች ገደለ፡፡
16ሳምሶንም እንዲህ አለ፣ “በአህያ መንጋጋ ክምር በክምር ላይ አድርጌአቸዋለሁ፣ በአህያ መንጋጋ አንድ ሺህ ሰዎች ገድያለሁ፡፡”
17ሳምሶንም መናገሩን በፈጸመ ጊዜ፣ የአህያ መንጋጋውን ከእጁ ጣለው፣ ያም ስፍራ ራማትሌሒ ተብሎ ተጠራ፡፡
18ሳምሶን በጣም ተጠምቶ ነበርና ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ጮኸ፣ “አንተ ይህን ታላቅ ድል ለአገልጋይህ ሰጥተሃል፣ ነገር ግን አሁን በጥም እሞታለሁ፣ ባልተገረዙትም ሰዎች እጅ እወድቃለሁ፡፡”
19እግዚአብሔርም በሌሒ ያለውን ክፍት ስፍራ ሰንጥቆ ከፈተው፣ ከእርሱም ውኃ ወጣ፡፡እርሱም በጠጣ ጊዜ፣ ብርታቱ ተመለሰና ተጠናከረ፡፡ ስለዚህ የዚያ ቦታ ስም ዓይንሀቆሬ ተብሎ ተጠራ፣ እስከ ዛሬ ድረስ በሌሒ ይገኛል፡፡
20ሳምሶን በፍልስጥኤማውያን ዘመን በእስራኤል ላይ ለሀያ ዓመት ፈረደ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።