መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መሳፍንት 14

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ሳምሶንም ወደ ተምና ወረደ፣ በዚያም ከፍልስጥኤማውያን ሴቶች ልጆች አንዲት ሴት አየ፡፡
2ከዚያ በተመለሰ ጊዜ፣ ለአባቱና ለእናቱ እንዲህ ሲል ነገራቸው፣ “በተምና ከፍልስጥኤማውያን ሴቶች ልጆች መካከል አንዲት ሴት አየሁ፡፡ ሚስቴ እንድትሆነኝ አሁን እርስዋን አምጡልኝና አጋቡኝ፡፡
3ነገር ግን እንዲህ አሉት፣ “ከዘመዶችህ ሴቶች ልጆች ወይም ከሕዝባችን ሁሉ መካከል ሴት የለምን? ካልተገረዙት ከፍልስጥኤማውያን ሚስት ለመውሰድ ትሄሄዳለህን?” ሳምሶንም ለአባቱ እንዲህ አለው፣ “እርስዋን አምጣልኝ፣ እርስዋን ባየኋት ጊዜ ደስ አሰኝታኛለችና፡፡”
4ነገር ግን አባቱና እናቱ ይህ ነገር የመጣው ከእግዚአብሔር እንደሆነ አላወቁም፣ እርሱ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ግጭት ለመፍጠር ይፈልግ ነበርና፡፡ በዚያን ጊዜ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ይገዙ ነበርና፡፡
5ከዚያም ሳምሶን ከአባቱና ከእናቱ ጋር ወደ ተምና ወረዱ፣ እነርሱም በተምና ወዳለው ወደ ወይኑ አትክልት ስፍራ መጡ፡፡ ከዚያም ከአንበሳ ደቦሎች መካከል አንዱ ተነስቶ መጣና በእርሱ ላይ አገሳበት፡፡
6የእግዚአብሔር መንፈስ በድንገት በእርሱ ላይ ወረደ፣ ትንሽ የፍየል ጠቦት እንደሚቆራርጥ እንዲሁ አንበሳውን በቀላሉ ቈራረጠው፣ በእጁም ምንም ነገር አልያዘም ነበር፡፡ ነገር ግን ያደረገውን ነገር ለአባቱ ወይም ለእናቱ አልነገራቸውም፡፡
7እርሱም ሄደና ከሴቲቱ ጋር ተነጋገረ፣ እርስዋንም ባያት ጊዜ ሳምሶንን ደስ አሰኘችው፡፡
8ከጥቂትም ቀን በኋላ ሊያገባት ተመለሰ፣ የአንበሳውንም በድን ያይ ዘንድ ከመንገድ ዘወር አለ፡፡ በአንበሳ በድን ትራፊ ውስጥ የንብ መንጋ ሰፍሮበት ነበር፣ ማርም ነበረበት፡፡
9ማሩንም በእጁ ወስዶ መንገድ ለመንገድ እየበላ ሄደ፡፡ ወደ አባቱና ወደ እናቱ በመጣ ጊዜ፣ ለእነርሱም ሰጣቸውና እነርሱም በሉ፡፡ ነገር ግን ማሩን የወሰደው ከአንበሳ በድን ትራፊ ውስጥ እንደ ሆነ አልነገራቸውም፡፡
10የሳምሶን አባትም ሴቲቱ ወደ ነበረችበት ወረደ፣ ሳምሶንም በዚያ ግብዣ አደረገ፣ ይህን ማድረግ የወጣት ወንዶች ወግ ነበርና፡፡
11የእርስዋ ዘመዶች ባዩት ጊዜ፣ ከእርሱ ጋር ይሆኑ ዘንድ ሌሎች ሠላሳ ጓደኞች አመጡለት፡፡
12ሳምሶንም ለእነርሱ እንዲህ አላቸው፣ “አሁን እንቆቅልሽ ልንገራችሁ፡፡ ከእናንተ ውስጥ አንዱ ሰው እንቆቅልሹን ማግኘት ቢችልና በሰባቱ የግብዣ ቀኖች ውስጥ መልሱን ቢነግረኝ፣ ሠላሳ የቀጭን በፍታ ቀሚስና ሠላሳ የክት ልብስ እሰጠዋለሁ፡፡
13ነገር ግን እናንተ መልሱን ልትነግሩኝ ካልቻላችሁ፣ ሠላሳ የቀጭን በፍታ ቀሚስና ሠላሳ የክት ልብስ ትሰጡኛላችሁ፡፡” እነርሱም እንዲህ አሉት፣ “እንሰማው ዘንድ እንቆቅልሽህን ንገረን፡፡”
14እርሱም እንዲህ አላቸው፣ “ከበላተኛው ውስጥ መብል ወጣ፤ ከብርቱም ውስጥ ጣፋጭ ወጣ፡፡” ነገር ግን የእርሱ እንግዶች በሦስት ቀን ውስጥ መልሱን ሊያገኙት አልቻሉም፡፡
15በአራተኛውም ቀን ለሳምሶን ሚስት እንዲህ አሏት፣ “የእንቈቅልሹን መልስ እንዲነግረን ባልሽን አግባቢልን፣ አለዚያ ግን እንቺንና የአባትሽን ቤት በእሳት እናቃጥላለን፡፡ ወደዚህ የጠራችሁን ድሃ ልታደርጉን ነውን፡፡”
16የሳምሶን ሚስት በፊቱ ማልቀስ ጀመረች፤ እንዲህም አለችው፣ “ይህን ሁሉ ያደረግኸው እኔን ስለምትጠላኝ ነው! አንተ አትወደኝም፡፡ ከሕዝቤ ውስጥ ለአንዳንዶቹ እንቈቅልሽ ነግረሃቸዋል፣ ነገር ግን መልሱን ለእኔ አልነገርኸኝም፡፡” ሳምሶንም እንዲህ አላት፣ “ወደዚህ ተመልከቺ፣ ለአባቴና ለእናቴ ካልነገርኋቸው፣ ለአንቺ ልነግርሽ ይገባልን?”
17ግብዣቸው በሚቆይበት በሰባቱም ቀናት ውስጥ በፊቱ አለቀሰች፡፡ መልሱንም በሰባተኛው ቀን ነገራት ምክንቱም እጅግ በጣም አጥብቃ ስለነዘነዘችው ነው፡፡ መልሱንም ለሕዝቧ ዘመዶች ነገረቻቸው፡፡
18በሰባተኛው ቀን ፀሐይ ከመግባትዋ በፊት የከተማይቱ ሰዎች እንዲህ አሉት፣ “ከማር የበለጠ የሚጣፍጥ ምንድን ነው? ከአንበሳስ የበለጠ የሚበረታ ምንድን ነው?” ሳምሶንም እንዲህ አላቸው፣ “በጊደሬ ባታርሱ ኖሮ፣ ለእንቈቅልሼ መልስ ባላገኛችሁ ነበር፡፡”
19በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በድንገት በሳምሶን ላይ በኃይል ወረደ፡፡ ሳምሶንም ወደ አስቀሎና ወረደና ከሕዝቡ መካከል ሠላሳ ሰዎችን ገደለ፡፡ እርሱም የለበሱትን ሁሉ ከገፈፈ በኋላ ልብሳቸውን በሙሉ ወስዶ እንቈቅልሹን ለመለሱለት ሰዎች ሰጣቸው፡፡ እርሱም በጣም ተናደደና ወደ አባቱ ቤት ወጣ፡፡
20የሳምሶን ሚስት ግን በጣም ቅርብ ለሆነው ጓደኛው ተሰጠች፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።