1የእስራኤልም ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ስራ እንደ ገና ሠሩ፣ እርሱም ፍልስጥኤማውያን በእነርሱ ላይ ለአርባ ዓመት እንዲገዙ ፈቀደላቸው፡፡
2ከዳን ቤተሰብ የሆነ ስሙም ማኑሄ የሚባል አንድ የጾርዓ ሰው ነበረ፡፡ ሚስቱም መካን ስለነበረች ልጅ አልወለደችም፡፡
3የእግዚአብሔርም መልአክ ለሴቲቱ ተገልጦ እንዲህ አላት፣ “ተመልከቺ፣ አንቺ መካን ነበርሽ፣ ልጅም አልወለድሽም፣ ነገር ግን ትፀንሻለሽ፣ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፡፡
4አሁንም የወይን ጠጅ ወይም የሚያሰክር ጠንካራ መጠጥ እንዳትጠጪ ተጠንቀቂ፣ ሕጉ ርኩስ እንደሆነ የገለጸውን ማንኛውንም ምግብ አትብዪ፡፡
5ተመልከቺ፣ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፡፡ ልጁ ከአንቺ ማኅፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ስለሚሆን በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፡፡ እርሱም እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን ጉልበት ማዳን ይጀምራል፡፡
6የዚያን ጊዜ ሴቲቱ ወደ ባልዋ መጥታ እንዲህ ብላ ነገረችው፣ “አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፣ መልኩም እንደ እግዚአብሔር መልአክ የሚመስል ነበረ፣ በጣምም አስደነገጠኝ፡፡ ከወዴት እንደ መጣ አልጠየቅሁትም፣ እርሱም ስሙን አልነገረኝም፡፡
7እርሱም እንዲህ አለኝ፣ ‘ተመልከቺ! ትፀንሻለሽ፣ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፡፡ ስለዚህ ልጁ ከአንቺ ማኅፀን ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ስለሚሆን የወይን ጠጅ ወይም የሚያሰክር ጠንካራ መጠጥ እንዳትጠጪ፣ ሕጉ ርኩስ እንደሆነ የገለጸውን ማንኛውንም ምግብ አትብዪ፡፡’”
8ከዚያም ማኑሄ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸለየ፣ “ጌታ ሆይ፣ አሁን በቅርቡ ለሚወለደው ልጅ ምን ማድረግ እንዳለብን እንዲያስተምረን እባክህ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው እንደገና ወደ እኛ ይምጣ፡፡”
9እግዚአብሔርም የማኑሄን ጸሎት መለሰ፣ የእግዚአብሔርም መልአክ እንደ ገና ወደ ሴቲቱ በእርሻ ውስጥ ተቀምጣ ሳለች መጣ፡፡ ነገር ግን ባልዋ ማኑሄ ከእርስዋ ጋር አልነበረም፡፡
10ስለዚህ ሴቲቱም ፈጥና ሮጠችና ለባልዋ ነገረችው፣ “ተመልከት! በሌላኛው ቀን ወደ እኔ የመጣው ሰው እንደገና ተገለጠልኝ፡፡”
11ማኑሄም ተነሳና ሚስቱን ተከተላት፡፡ ወደ ሰውዮውም በመጣ ጊዜ እንዲህ አለው፣ “ከሚስቴ ጋር የተነጋገርህ ሰው አንተ ነህን?” ሰውየውም፣ “እኔ ነኝ” አለው፡፡
12ስለዚህ ማኑሄ እንዲህ አለ፣ “አሁንም ቃሎችህ እውነት ይሁኑ፡፡ ነገር ግን ልጁ የሚመራው በምንድን ነው፣ እኛስ ለእርሱ የምንሰራው ምንድን ነው?”
13የእግዚአብሔርም መልአክ ለማኑሄ እንዲህ አለው፣ “እርስዋ የነገርኋትን ነገር ሁሉ በጥንቃቄ ማድረግ አለባት፡፡
14ከወይን ከሚወጣው ማንኛውንም ነገር አትብላ፣ የወይን ጠጅ ወይም የሚያሰክር ሌላ ጠንካራ መጠጥ አትጠጣ፤ ሕጉ ርኩስ ነው ብሎ የገለጸውን ማንኛውንም ምግብ አትብላ፡፡ እኔ እንድታደርገው ያዘዝኋትን ማንኛውንም ነገር መታዘዝ አለባት፡፡
15ማኑሄም ለእግዚአብሔር መልአክ እንዲህ አለው፣ “ለአንተ የፍየል ጠቦት ለማዘጋጀት ጊዜ እናገኝ ዘንድ፣ እባክህ ለአጭር ጊዜ ቆይ፡፡”
16የእግዚአብሔርም መልአክ ለማኑሄ እንዲህ አለው፣ “ብቆይም እንኳ፣ መብልህን አልበላም፡፡ነገር ግን የሚቃጠል መሥዋዕት የምታዘጋጅ ከሆነ፣ ያንን ለእግዚአብሔር አቅርበው፡፡” ማኑሄ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር፡፡
17ማኑሄም ለእግዚአብሔር መልአክ እንዲህ አለው፣ “የተናገርሃቸው ቃሎች እውነት በሆኑ ጊዜ እናከብርህ ዘንድ ስምህ ማን ነው?”
18የእግዚአብሔርም መልአክ እንዲህ አለው፣ “ስሜን ለምን ትጠይቃለህ? ስሜ ድንቅ ነው!”
19ስለዚህ ማኑሄም የፍየሉን ጠቦት ከእህል ቍርባን ጋር ወሰደና በድንጋይ ላይ ለእግዚአብሔር አቀረበው፡፡ ማኑሄና ሚስቱ እያዩ እርሱ አስደናቂ ነገር አደረገ፡፡
20ነበልባሉም ከመሠዊያው ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ፣ የእግዚአብሔር መልአክ በመሠዊያው ነበልባል ውስጥ ወደ ላይ ዐረገ፡፡ ማኑሄና ሚስቱም ይህን ተመለከቱና በግምባራቸው ምድር ላይ ተደፉ፡፡
21የእግዚአብሔርም መልአክ ላማኑሄ ወይም ለሚስቱ እንደገና አልተገለጠም፡፡ ያን ጊዜም ማኑሄ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አወቀ፡፡
22ማኑሄም ለሚስቱ እንዲህ አላት፣ “እግዚአብሔርን ስላየን በእርግጠኝነት እንሞታለን፡፡”
23ነገር ግን ሚስቱ እንዲህ አለችው፣ “እግዚአብሔር ሊገድለን ቢፈልግ ኖሮ፣ ለእርሱ ያቀረብነውን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ባልተቀበለን ነበር፡፡ ይህንም ነገር ሁሉ ባላሳየን ነበር፣ በዚህ ጊዜ እንዲህ ያሉ ነገሮችንም እንድንሰማ ባላደረገን ነበር፡፡”
24ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሴቲቱ ወንድ ልጅ ወለደች፣ ስሙንም ሳምሶን ብላ ጠራችው፡፡ ልጁም አደገ እግዚአብሔርም ባረከው፡፡
25የእግዚአብሔርም መንፈስ እርሱን በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በዳን ሰፈር ውስጥ ያነቃቃው ጀመር፡፡