1ወደ ኤፍሬም ሰዎችም ጥሪ ደረሰ፤ በጻፎን በኩል ተሻግረው ዮፍታሔን፣ “ከአሞን ሕዝብ ጋር ለመዋጋት ስታልፍ ከአንተ ጋር እንድንሄድ ያልጠራኸን ለምድን ነው? ቤትህን በአንተ ላይ እናቃጥለዋለን” አሉት፡፡
2ዮፍታሔም እንዲህ አላቸው፣ “እኔና ሕዝቤ ከአሞን ሕዝብ ጋር በታላቅ ጦርነት ውስጥ ነበርን፡፡ በጠራኋችሁም ጊዜ ከእነርሱ አላዳናችሁኝም፡፡
3እናንተም እንዳላዳናችሁኝ ባየሁ ጊዜ፣ ሕይወቴን በራሴ ብርታት አስቀምጬ በአሞን ሕዝብ ላይ ለመዋጋት አለፍሁ፣ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ድል ሰጠኝ፡፡ ዛሬ እኔን ለመውጋት ለምን መጣችሁ?
4ዮፍታሔም የገለዓድን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበና ከኤፍሬምም ጋር ተዋጋ፡፡ የገለዓድም ሰዎች የኤፍሬምን ሰዎች ወጓቸው ምክንቱም፣ “እናንተ ገለዓዳውያን በኤፍሬም ውስጥ ሸሽታችሁ የተጠጋችሁ፣ በኤፍሬምና በምናሴ ውስጥ ጥገኞች የሆናችሁ ናችሁ” ይሏቸው ነበርና፡፡
5ገለዓዳውያንም ወደ ኤፍሬም የሚወስደውን የዮርዳኖስን መሻገሪያ ያዙባቸው፡፡ አምልጦ የሚሸሽ የኤፍሬም ሰው፣ “ወንዙን ተሻግሬ ልለፍ” ባለ ጊዜ፣ የገለዓድ ሰዎች ደግሞ እንዲህ ይሉታል፣ “አንተ ኤፍሬማዊ ነህን?” እርሱም፣ “አይደለሁም” ቢል፣
6እነርሱም “ሺቦሌት በል” ይሉታል፡፡ እርሱም “ሲቦሌት” ብሎ ከተናገረ (ምክንያቱም እርሱ ቃሉን አጥርቶ መናገር አይችልምና) ፣ ገለዓዳውያን እርሱን ይዘው በዮርዳኖስ መሻገሪያ ላይ ይገድሉታል፡፡ በዚያም ጊዜ አርባ ሁለት ሺህ ኤፍሬማውያን ተገደሉ፡፡
7ዮፍታሔም በእስራኤል ላይ ለስድስት ዓመት እንደ ፈራጅ አገለገለ፡፡ ከዚያም ገለዓዳዊውም ዮፍታሔ ሞተ፣ ከገለዓድ ከተሞችም በአንዱ ተቀበረ።
8ከእርሱም በኋላ የቤተ ልሔሙ ኢብጻን በእስራኤል ላይ እንደ ፈራጅ አገለገለ፡፡
9እርሱም ሠላሳ ወንዶች ልጆች ነበሩት፡፡ ሠላሳ ሴቶች ልጆችንም ወደ ውጭ በትዳር ለሌሎች ሰጠ፣ ሠላሳ ሴቶች ልጆችን ደግሞ ከሌሎች ሰዎች በትዳር ለወንድ ልጆቹ አመጣ። በእስራኤልም ላይ ለሰባት ዓመት ፈረደ።
10ኢብጻንም ሞተ፣ በቤተ ልሔምም ተቀበረ፡፡
11ከእርሱም በኋላ ዛብሎናዊው ኤሎም በእስራኤል ላይ እንደ ፈራጅ አገለገለ፡፡ እርሱም በእስራኤል ላይ ለአሥር ዓመት ፈረደ፡፡
12ዛብሎናዊውም ኤሎም ሞተ፣ በዛብሎንም ምድር ባለችው በኤሎም ተቀበረ፡፡
13ከእርሱም በኋላ የጲርዓቶናዊው የሂሌል ልጅ ዓብዶን በእስራኤል ላይ እንደ ፈራጅ አገለገለ፡፡
14እርሱም አርባ ወንዶች ልጆችና ሠላሳ ወንዶች የልጅ ልጆች ነበሩት፡፡ በሰባ አህያዎች ላይ ይጋልቡ ነበር፣ እርሱም በእስራኤል ላይ ለስምንት ዓመት ፈረደ፡፡
15የጲርዓቶናዊውም የሂሌል ልጅ ዓብዶን ሞተ፣ በተራራማውም በአማሌቃውያን አገር በኮረብታማው በኤፍሬም አገር ውስጥ ባለችው በጲርዓቶን ውስጥ ተቀበረ፡፡