1ገለዓዳዊውም ዮፍታሔ ኃያል ተዋጊ ነበር፣ ነገር ግን የጋለሞታ ሴት ልጅ ነበረ፡፡ አባቱም ገለዓድ ነበረ፡፡
2የገለዓድም ሚስት ደግሞ ሌሎች ወንዶች ልጆችን ወለደችለት፡፡ የሚስቱ ልጆች ባደጉ ጊዜ፣ ዮፍታሔን ቤቱን ለቅቆ እንዲወጣ አስገደዱት፣ እንዲህም አሉት፡- “አንተ ከቤተሰባችን ምንም ነገር አትወርስም፡፡ አንተ የሌላ ሴት ልጅ ነህ፡፡”
3ስለዚህ ዮፍታሔ ከወንድሞቹ ፊት ሸሸና በጦብ ምድር ተቀመጠ፡፡ ስርዓት አልበኛ ሰዎችም ተከተሉት፣ ተሰብስበውም ከእርሱ ጋር ሄዱ፡፡
4ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ የአሞን ሰዎች ከእስራኤል ጋር ውጊያ አደረጉ፡፡
5የአሞንም ሰዎች ከእስራኤል ጋር ውጊያ ባደረጉ ጊዜ፣ የገለዓድ ሽማግሌዎች ዮፍታሔን ከጦብ ምድር ለማምጣት ሄዱ፡፡
6ዮፍታሔንም፣ “ና፣ ከአሞን ሰዎች ጋር እንድንዋጋ አለቃችን ሁን” አሉት፡፡
7ዮፍታሔም ለገለዓድ ሽማግሌዎች እንዲህ አላቸው፣ “እናንተ ጠልታችሁኛል፣ የአባቴንም ቤት ትቼ እንድሄድ አስገድዳችሁኛል፡፡ አሁን በተቸገራችሁ ጊዜ ለምን ወደ እኔ መጣችሁ?”
8የገለዓድም ሽማግሌዎችም ለዮፍታሔ፣ “አሁን ወደ አንተ የተመለስነው ለዚህ ነው፤ ከእኛ ጋር ና፣ ከአሞንም ሰዎች ጋር ተዋጋ፣ ከዚያም በኋላ በገለዓድ በሚኖሩት ሰዎች ሁሉ ላይ መሪ ትሆናለህ” አሉት፡፡
9ዮፍታሔም ለገለዓድ ሽማግሌዎች፣ “ከአሞን ሰዎች ጋር እንድዋጋ እንደገና ወደ ቤቴ ከመለሳችሁኝ፣ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ድል ከሰጠን መሪያችሁ እሆናለሁ” አላቸው፡፡
10የገለዓድ ሽማግሌዎችም ለዮፍታሔ፣ “እንደተናገርነው የማናደርግ ከሆነ እግዚአብሔር በእኛ መካከል ምስክር ይሁን” አሉት፡፡
11ስለዚህ ዮፍታሔ ከገለዓድ ሽማግሌዎች ጋር ሄደ፣ ሕዝቡም በላያቸው ላይ መሪና የጦር አዛዥ አደረጉት፡፡ እርሱ በምጽጳ በእግዚአብሔር ፊት በነበረ ጊዜ፣ ዮፍታሔ የገባውን ቃል ኪዳን ሁሉ ደገመው፡፡
12ዮፍታሔም ወደ አሞን ሰዎች ንጉሥ እንዲህ በማለት መልእክተኞችን ላከ፡- “በእኛ መካከል ያለው ጠብ ምንድን ነው? ምድራችንን ለመውሰድ በጦር ለምን መጣህ?”
13የአሞንም ሰዎች ንጉሥም ለዮፍታሔ መልክተኞች “እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ ከአርኖን ጀምሮ እስከ ያቦቅና እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ምድሬን ወስደዋል፡፡ አሁን እነዚህን መሬቶች በሰላም መልሱልኝ” ብሎ መለሰላቸው፡፡
14ዮፍታሔም ወደ አሞን ሰዎች ንጉሥ መልክተኞችን እንደ ገና ላከ፣
15እንዲህም አለው፣ “ዮፍታሔ የሚለው ይህንን ነው፡- እስራኤል የሞዓብን ምድር የአሞንንም ሰዎች ምድር አልወሰደም፣
16ነገር ግን ከግብፅ በወጡ ጊዜ፣ እስራኤል በምድረ በዳ በኩል ወደ ቀይ ባሕር ከዚያም ወደ ቃዴስ ሄዱ፣
17እስራኤል ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ እንዲህ በማለት መልእክተኞችን ላኩ፣ ‘በምድርህ እንድናልፍ እባክህ ፍቀድልን፣’ ነገር ግን የኤዶምያስ ንጉሥ አልሰማም፡፡ እንዲሁም ወደ ሞዓብ ንጉሥ መልእክተኞች ላኩ፣ እርሱም አልፈቀደም፡፡ ስለዚህ እስራኤል በቃዴስ ተቀመጠ፡፡
18እነርሱም በምድረ በዳ በኩል ሄዱና ከኤዶምያስና ከሞዓብ ምድር ተመለሱ፣ በሞዓብም ምድር በምሥራቅ በኩል ሄዱ፣ በአርኖንም ማዶ ሰፈሩ፡፡ ነገር ግን ወደ ሞዓብ ክልል ውስጥ አልገቡም፣ አርኖን የሞዓብ ድንበር ነበረና፡፡
19እስራኤልም በሐሴቦን ውስጥ ገዥ ወደነበረው ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልክተኞችን ላከ፤ እስራኤልም ‘እባክህ፣ በምድርህ በኩል ወደ ስፍራችን እንድናልፍ ፍቀድልን’ አለው፡፡
20ነገር ግን ሴዎን እስራኤል በድንበሩ እንዲያልፍ አላመነውም፡፡ ስለዚህ ሴዎን ሰራዊቱን ሁሉ ሰበሰበና ወደ ያሀጽ ተንቀሳቀሰ፣ በዚያም ከእስራኤል ጋር ተዋጋ፡፡
21የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔርም ለእስራኤል በሴዎን ላይ ድል ሰጠውና ሕዝቡን ሁሉ በቁጥጥራቸው ስር እንዲሆኑ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ ስለዚህም እስራኤል በዚያች አገር ተቀምጠው የነበሩትን የአሞራውያንን አገር ሁሉ ወሰዱ፡፡
22በአሞራውያን ክልል ውስጥ የነበረውን ሁሉንም ነገር ወሰዱ፣ ከአርኖንም እስከ ያቦቅ ድረስ፣ ከምድረ በዳውም እስከ ዮርዳኖስ ድረስ፡፡
23ያንጊዜ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር አሞራውያንን ከሕዝቡ ከእስራኤል ፊት አስወጣቸው፣ ታዲያ አንተ አሁን ምድራቸውን ልትወስድ ይገባልን?
24አምላክህ ካሞሽ የሚሰጥህን ምድር አትወስድምን? ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካችን የሰጠንን ምድር ሁሉ እንወስዳለን፡፡
25አሁን አንተ ከሞዓብ ንጉሥ ከሴፎር ልጅ ከባላቅ በእውነት ትሻላለህን? እርሱ ከእስራኤል ጋር ከቶ ክርክር ነበረውን? ከእነርሱ ጋር ጦርነት አካሂዷልን?
26እስራኤል በሐሴቦንና በቀበሌዎችዋ፣ በአሮዔርና በቀበሌዎችዋ፣ በአርኖንም ዳርቻ ባሉት ከተሞች ሁሉ ለሦስት መቶ ዓመት ሲኖር በነበረበት ጊዜ፣ ለምን ታዲያ በዚያን ጊዜ መልሳችሁ አልወሰዳችኋቸውም ነበር?
27እኔ አልበደልሁህም ነገር ግን አንተ እኔን በመውጋት እየበደልከኝ ነው፡፡ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በእስራኤል ሰዎችና በአሞን ሰዎች መካከል ዛሬ ይፈርዳል፡፡
28ነገር ግን የአሞን ሰዎች ንጉሥ ዮፍታሔ የላከበትን ማስጠንቀቂያ አልተቀበለም፡፡
29ያን ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በዮፍታሔ ላይ መጣ፣ እርሱም በገለዓድና በምናሴ አለፈ፣ በገለዓድ ባለው ምጽጳም አለፈ፣ ከዚያም በገለዓድ ካለው ምጽጳ ወደ አሞን ሰዎች አለፈ፡፡
30ዮፍታሔም ለእግዚብሔር እንዲህ ሲል ስእለት ተሳለ፡- “በአሞንን ሰዎች ላይ ድልን ብትሰጠኝ፣
31ከአሞን ሰዎች በሰላም በተመለስሁ ጊዜ እኔን ሊያገኘኝ ከቤቴ በር የሚወጣው ማንኛውም ለእግዚአብሔር ይሆናል፣ እርሱንም ለሚቃጠል መሥዋዕት አቀርበዋለሁ፡፡
32ስለዚህ ዮፍታሔ እነርሱን ለመውጋት ወደ አሞን ሰዎች አለፈ፣ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ድል ሰጠው፡፡
33እርሱም ከአሮዔርም እስከ ሚኒት፣ እንደዚሁም እስከ አቤልክራሚም ድረስ ያሉ ሀያ ከተሞችን ወጋቸው፣ ታላቅ እልቂትም አደረሰባቸው፡፡ ስለዚህ የአሞን ሰዎች በእስራኤል ሰዎች ቁጥጥር ስር ሆኑ፡፡
34ዮፍታሄ ምጽጳ ወዳለው ቤቱ መጣ፣ በዚያም የእርሱ ልጅ ከበሮ ይዛ እያሸበሸበች ልታገኘው ወጣች፡፡ እርስዋም ብቸኛ ልጁ ነበረች፣ ከእርስዋ ሌላ ወንድ ልጅም ይሁን ሴት ልጅ አልነበረውም፡፡
35እርስዋንም ባየ ጊዜ፣ ልብሱን ቀደደ እንዲህም አለ፡- “ወይኔ! ልጄ ሆይ! በኀዘን አደቀቅሽኝ፣ በእኔ ላይ ጭንቅ ያመጣብኝ ሰው ሆንሽብኝ! ለእግዚአብሔር ስእለት ተስያለሁና፣ ቃሌን ማጠፍ በፍጹም አልችልም፡፡”
36እርስዋም እንዲህ አለችው፡- “አባቴ ሆይ፣ ለእግዚአብሔር ስእለት ተስለሃል፣ ቃል የገባኸውን ሁሉ በእኔ ላይ አድርግብኝ፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር በጠላቶችህ በአሞናውያን ላይ ተበቅሎልሃልና፡፡”
37አርስዋም ለአባትዋ እንዲህ አለች፡- “ይህ ቃል ለእኔ ይደረግልኝ፡፡ ይህንን አካባቢ እንድለቅና ወደ ታች ወደ ኮረብታዎቹ እንድወርድ፣ ከጓደኞቼም ጋር ስለ ድንግልናየ እንዳለቅስ ለሁለት ወራቶች ያህል ብቻየን እንድሆን ፍቀድልኝ፡፡
38እርሱም፣ “ሂጂ” አለ፡፡ ለሁለት ወራትም አሰናበታት፡፡ እርስዋም ትታው ሄደች፣ ከባልንጀሮችዋም ጋር ስለ ድንግልናዋ በኮረብታዎቹ ላይ አለቀሱ፡፡
39በሁለት ወር መጨረሻ ላይ ወደ አባትዋ ተመለሰች፣ እርሱም ቃል እንደገባው እንደ ስእለቱ አደረገባት፡፡ እርስዋም ከወንድ ጋር ተኝታ አታውቅም፣ ይህም በእስራኤል ዘንድ ልማድ ሆነ፣
40የእስራኤል ሴቶች ልጆች በየዓመቱ፣ ለአራት ቀናት፣ የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ሴት ልጅ ታሪክ እየተናገሩ ያስቡአታል፡፡