1በእናንተ መከከል ያለው ፀብና ጭቅጭቅ ከየት የመጣ ነው? በውስጣችሁ ውጊያ ከገጠሙት ክፉ ምኞቶቻችሁ የመጣ አይደለምን?
2የሌላችሁን ትመኛላችሁ። ትገድላላችሁ፤ ማግኘት ያልቻላችሁትን በብርቱ ታሳድዳላችሁ። ትጣላላችሁ፤ ትዋጋላችሁ፤ ይሁን እንጂ፣ ከእግዚአብሔር ስለማትለምኑ አታገኙም።
3ትለምናላችሁ ግን አትቀበሉም፤ ምክንያቱም ክፉ ምኞቶቻችሁን ለማሳካት ክፉ ነገሮችን ስለምትለምኑ ነው።
4እናንት አመንዝሮች! የዓለም ወዳጅ መሆን፣ የእግዚአብሔር ጠላት መሆን እንደ ሆነ አታውቁም? ስለዚህ ማንም የዓለም ወዳጅ መሆን ቢፈልግ፣ የእግዚአብሔር ጠላት ይሆናል።
5ወይስ እግዚአብሔር እኛ ውስጥ ያኖረው መንፈስ ለእርሱ ብቻ እንድንሆን አብዝቶ ይቀናል የሚለው የመጽሐፍ ቃል በከንቱ የተነገረ ይመስላችኋል?
6እግዚአብሔር ግን አብዝቶ ጸጋውን ይሰጣል፤ መጽሐፍ፣ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” የሚለው በዚህ ምክንያት ነው።
7ስለዚህ፣ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ እርሱም ከእናንተ ይሸሻል።
8ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፣ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች እጆቻችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ።
9እዘኑ፤ አልቅሱ፤ ጩኹ! ሳቃችሁን ወደ ሐዘን፣ ደስታችሁን ወደ ትካዜ ለውጡ።
10በጌታ ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ያደርጋችኋል።
11ወንድሞች ሆይ፣ እርስ በርስ አትወነጃጀሉ። ወንድሙን የሚወነጅልና በወንድሙ ላይ የሚፈርድ ሕጉ ላይ ክፉ ይናገራል፤ በእግዚአብሔርም ሕግ ላይ ይፈርዳል። ሕጉ ላይ የምትፈርዱ ከሆነ፣ ፈራጆች እንጂ፣ ሕጉን አድራጊዎች አይደላችሁም።
12ሕጉን የሰጠና በሕጉም የሚፈርድ፣ ማዳንም መግደልም የሚቻለው አንዱ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ታዲያ፣ በባልንጀራህ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?
13“ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህ አገር እንሄዳለን፤ እዚያ አንድ ዓመት እንቆያለን፤ ነግደን እናተርፋለን” የምትሉ እናንተ ሰዎች ስሙ።
14ነገ የሚሆነውን የሚያውቅ ማን ነው? ሕይወታችሁስ ምንድን ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ ጭጋግ አይደላችሁምን?
15ይልቁንም፣ “ጌታ ቢፈቅድ እንኖራለን፤ ይህን ወይም ያንን እናደርጋለን” ማለት ይኖርባችኋል።
16አሁን ግን በዕቅዶቻችሁ ትመካላችሁ። እንዲህ ያለው ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው።
17ስለዚህ መልካም የሆነውን ማድረግ እንዳለበት እያወቀ ለማያደርግ ለዚያ ሰው ኃጢአት ይሆንበታል።