1እንግዲህ እናንተ ሀብታሞች ስለሚመጡባችሁ ክፉ ነገሮች አልቅሱ ዋይ ዋይም በሉ።
2ሀብታችሁ ሻግቶአል፤ ልብሳችሁንም ብል በልቶታል።
3ወርቃችሁና ብራችሁ ዝጎአል፤ ዝገቱም እናንተ ላይ ይመሰክራል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላዋል። ለመጨረሻው ቀን ሀብታችሁን አከማችታችኋል።
4ልብ በሉ፤ እርሻችሁን ላጨዱ ሠራተኞች ያልከፈላችሁት ደመወዝ ይጮኻል! የአጫጆቹም ጩኸት የሠራዊት ጌታ ጆሮ ደርሶአል።
5በምድር ላይ በምቾትና በመንደላቀቅ ኖራችኋል። ለዕርድ ቀን ልባችሁን አወፍራችኋል።
6እናንተን ያልተቃወመውን ጻድቅ ሰው ኮንናችሁታል፤ ገድላችሁታል።
7ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፣ የመጀመሪያውና የኋለኛው ዝናብ እስኪመጣ ድረስ የምድርን ፍሬ በትዕግሥት እንደሚጠብቅ ገበሬ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ።
8እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ ልባችሁን አዘጋጁ፤ ምክንያቱም የጌታ መምጫ ቅርብ ነው።
9ወንድሞች ሆይ፤ እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ። ልብ በሉ፤ ፈራጁ በሩ ላይ ቆሞአል።
10በጌታ ስም የተናገሩ ነቢያትን መከራና ትዕግሥት እንደ ምሳሌ ውሰዱት።
11ልብ በሉ፤ በትዕግሥት የጸኑትን፣ “የተባረኩ” እንላቸዋለን። ስለ ኢዮብ ትዕግሥት ሰምታችኋል፤ ጌታ ለኢዮብ የነበረውንም ዓላማ ታውቃላችሁ፤ ጌታ እጅግ ሩኅሩኅና መሐሪ ነው።
12ወንድሞቼ ሆይ፣ ከሁሉም በላይ አትማሉ፤ በሰማይም ሆነ በምድር ወይም በሌላ ነገር አትማሉ። ቃላችሁ “አዎን” ካላችሁ፣ “አዎን” ይሁን፤ “አይደለም” ካላችሁም፣ “አይደለም” ይሁን።
13በእናንተ መካከል መከራ የደረሰበት አለ? እርሱ ይጸልይ። ደስ ያለው አለ? እርሱ ይዘምር።
14በእናንተ መካከል የታመመ አለ? የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ይጥራ፤ እነርሱም በጌታ ስም ዘይት እየቀቡ ይጸልዩለት፤
15የእምነት ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሳል፤ ጌታም ያስነሣዋል። ኃጢአት አድርጎ ከሆነም እግዚአብሔር ይቅር ይለዋል።
16እንዲሁ ጌታ ከበሽታ ሊፈውስና ኃጢአትን ይቅር ሊል ስለሚችል ያደረጋችሁትን ኃጢአት በተመለከተ አንዳችሁ ለሌላችሁ ተናዘዙ፡፡ ጻድቃን ሰዎች ከጸለዩና አንድ ነገር እንዲያደርግላቸው ጌታን አጥብቀው ከጠየቁት፣ እግዚአብሔር ይገለጣል፤ ደግሞም በእርግጠኝነት ያን ነገር ያደርገዋል፡፡
17ነቢዩ ኤልያስ እንደኛው ያለ ሰው ቢሆንም፣ ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፡፡ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወራት ጊዜ ያህልም ዝናብ አልነበረም፡፡
18ከዚያም ዝናብ እንዲዘንብ እግዚአብሔርን እየለመነ ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ዝናብን ላከ፣ ተክሎችም ዐደጉና ሰብልን ሰጡ፡፡
19ወንድቼና እኅቶቼ ሆይ፥ ከእናንተ አንዱ ዕውነተኛውን የእግዚአብሔርን ቃል መልእክት መታዘዝ ቢያቆም፣ ከእናንተ አንዱ ያደርገው ዘንድ እግዚአብሔር ለዚያ ሰው የነገረውን ነገር በመንገር ሊያሳምነው ይገባል፡፡
20የሚያሳምነው ሰውም ኃጢአት እየሠራ የነበረውን ሰው ተናግሮ ስሕተት ከመሥራት እንዲመለስ ስላስቻለው፣ እግዚአብሔር ያንን ሰው ከመንፈሳዊ ሞት ያድነዋል፤ ደግሞም ብዙ የሆኑት ኃጢአቶቹን ይቅር ይልለታል፡፡