1ወንድሞች ሆይ፤ ለአንዳንዶች አድልዎ እያደረጋችሁ የክብር ጌታ የጌታችን አየሱስ ክርስቶስን እምነት እንከተላለን አትበሉ።
2የወርቅ ቀለበት ያደረገና የሚያማምሩ ልብሶች የለበሰ ወደ ስብሰባችሁ ሲገባና እንዲሁም አዳፋ ልብሶች የለበሰ ድኻ ቢገባ
3ትኵረታችሁ የሚያማምሩ ልብሶች የለበሰው ሰው ላይ ይሆንና፣ “እዚህ ደኅና ቦታ ላይ ተቀመጥ” ትሉታላችሁ፤ ድኻውን ግን፣ “እዚያ ቁም” ወይም “ከእግሬ በታች ተቀመጥ” ትሉታላችሁ
4ታዲያ፣ በመካከላችሁ አድልዎ ማድረጋችሁ አይደለምን፤ ደግሞስ በክፉ ዐሳብ የተያዛችሁ ፈራጆች መሆናችሁ አይደለምን?
5የተወደዳችሁ ወንድሞች ስሙ፤ በእምነት ባለ ጸጋ እንዲሆኑና፣ እርሱን ለሚወዱ ቃል የገባላቸውን መንግሥት እንዲወርሱ እግዚአብሔር የዚህ ዓለም ድኾችን አልመረጠምን?
6እናንተ ግን ድኾችን አዋረዳችሁ! የሚጨቁኗችሁ ባለ ጸጎች አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤት የሚጎትቱዋችሁስ እነርሱ አይደሉምን?
7የተጠራችሁበትን መልካም ስም የሚሳደቡ ባለ ጸጎቹ አይደሉምን?
8ይሁን እንጂ፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ተብሎ እንደ ተጻፈው የከበረውን ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ፤
9ለአንዳንዶች አድልዎ ብታደርጉ ግን፣ ኃጢአት ትሠራላችሁ፤ እንደ ሕግ ተላላፊዎችም ትቆጠራላችሁ።
10ምክንያቱም ሕጉን የሚፈጽም፣ በአንዱ ግን የሚሰናከል፣ ሕጉን ሁሉ እንደ ተላለፈ ይቆጠራል!
11“አታመንዝር” ያለው እግዚአብሔር፣ “አትግደልም” ብሎአልና። ባታመነዝር ሆኖም ግድያ ብትፈጽም፣ የእግዚአብሔርን ሕግ ተላልፈሃል።
12ስለዚህ ነጻ በሚያወጣው ሕግ እንደሚፈረድባቸው ሰዎች ተናገሩ፤ ደግሞም ታዘዙ።
13ምክንያቱም ምሕረት በማያደርጉ፣ ምሕረት የሌለበት ፍርድ ይመጣባቸዋል። ምሕረት ፍርድን ያሸንፋል!
14ወንድሞቼ ሆይ፣ አንድ ሰው እምነት እንዳለው ቢናገር፣ ሥራ ግን ባይኖረው ምን ይጠቅማል? ያ እምነት ሊያድነው ይችላልን?
15አንድ ወንድም ወይም እኅት ልብስና የዕለት ምግብ ባይኖራቸው
16ከእናንተ አንዱ፣ “በሰላም ሂዱ፤ አይብረዳችሁ፤ በደንብ ጥገቡ” ቢላቸው፤ ለአካል የሚያስፈልጉ ነገሮችን ግን ባትሰጧቸው፣ ምን ይጠቅማል?
17ሥራ የሌለው እምነትም እንዲሁ በራሱ የሞተ ነው።
18ምናልባትም አንዱ፣ “አንተ እምነት አለህ እኔ ደግሞ ሥራ አለኝ” ሥራ የሌለው እምነትህን አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይል ይሆናል።
19አንድ እግዚአብሔር መኖሩን ታምናለህ፤ ትክክል ነህ። አጋንንትም ይህን ያምናሉ፤ በፍርሃትም ይንቀጠቀጣሉ።
20አንተ ሞኝ፣ እምነት ያለ ሥራ ከንቱ መሆኑን ማወቅ ትፈልጋለህ?
21አባታችን አብርሃም፣ ልጁ ይስሐቅን መሠዊያው ላይ ባቀረበ ጊዜ በሥራ ጸድቆ አልነበረምን?
22እምነት በሥራው ታየ፤ በዚያው ሥራ እምነት ዓላማውን ፈጸመ።
23“አብርሃም እግዚአብሔርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት” የሚለው የመጽሐፍ ቃል ተፈጸመ። ስለዚህም አብርሃም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ።
24ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን፣ በሥራ እንደሚጸድቅ ታያለህ።
25በተመሳሳይ ሁኔታ ጋለሞታዪቱ ረዓብ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቅችምን?
26ከመንፈስ የተለዬ አካል ሙት እንደ ሆነ ሁሉ፣ ከሥራ የተለዬ እምነትም የሞተ ነው።