መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ያዕቆብ 1

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር እስረኛና አገልጋይ የሆነ ያዕቆብ በክርስቶስ ኢየሱስ ለሚያምኑና በመላው ዓለም ለተበተኑት ለአሥራ ሁለቱ ነገዶች ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡
2ወንድሞቼ ሆይ፣ በልዩ ልዩ ፈተናዎች ውስጥ ማለፋችሁን እጅግ ደስ እንደሚያሰኝ ነገር ቊጠሩት፡፡
3በፈተና ውስጥ ሳላችሁ በእግዚአብሔር ስታምኑ ይበልጥ ሌሎች ፈተናዎችን በትዕግሥት ለማሳለፍ የሚረዱዋችሁ መሆኑን ትረዳላችሁ፡፡
4ክርስቶስን በሁሉም መንገድ ትከተሉ ዘንድ እስከ መጨረሻው በፈተና ጽኑ፤ ያንጊዜ መልካም ማድረግ አይከብዳችሁም፡፡
5ከእናንተ አንዱ ምን ማድረግ እንዳለበት ማወቅ ከፈለገ፣ በሚጠይቀው ላይ ሳይቈጣ በልግሥና የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይጠይቅ፡፡
6እግዚአብሔርን ስትለምኑ፣ የምትጠይቁትን እንደሚሰጣችሁ እመኑ፤ መልስ እንደሚሰጣችሁና ሁልጊዜም እንደሚረዳችሁ አትጠራጠሩ፤ የሚጠራጠሩ ሰዎች እግዚአብሔርን ሊከተሉት አይችሉም፤ መጠራጠር ልክ ተመልሶ እንደሚመጣ፣ ደግሞም በዚያው አቅጣጫ መጓዝን እንደማይቀጥል የባሕር ማዕበል ያለ ነገር ነው፡፡
7በእርግጥ የሚጠራጠሩ ሰዎች የሚጠይቁትን ነገር ለመፈጸም እግዚአብሔር አንድ ነገር ሊያደርግ እንደሚችል አያምኑም፡፡
8እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን ለመከተል ወይም ላለመከተል ያልወሰኑ ናቸው፤ እነዚህም የሚናገሩትን ነገር የማያደርጉ ሰዎች ናቸው፡፡
9ድሀ የሆኑ አማኞች እግዚአብሔር ስላከበራቸው ደስ ሊሰኙ ይገባል፡፡
10ባለጠጋ የሆኑ አማኞችም እግዚአብሔር ትሑታን ስላደረጋቸው ደስ ሊሰኙ ይገባል፤ ልክ የበረሃ አበቦች እንደሚደርቁ ሁሉ፣ እነርሱም ሆኑ ሀብታቸው የሚያልፉ ናቸውና፡፡
11ፀሐይ በሚወጣ ጊዜ ሞቃታማ የሆነው ነፋስ ተክሎችን ያደርቃል፤ ደግሞም አበቦችን በምድር ላይ እንዲወድቁም ሆነ በውበታቸው እንዳይቀጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ባለ ጠጎች ልክ እንደሚሞቱ አበቦች ሁሉ ገንዘብን እየሰበሰቡ ሳሉ ይሞታሉ፡፡
12በመከራ የሚጸኑትን ሰዎች እግዚአብሔር ያከብራቸዋል፤ ለሚወድዱት ሁሉ ተስፋ እንደ ሰጠው ለዘላለም እንዲኖሩ በማድረግ ብድራታቸውን ይከፍላቸዋል፡፡
13በኃጢአት ስንፈተን እግዚአብሔር እየፈተነን ነው ብለን ልናስብ አይገባም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ክፉን እንድንሠራ አይፈልግምና፤ ክፉን እንዲያደርግ ማንንም አይፈትንምና፡፡
14እያንዳንዱ ሰው የሚፈተነው በራሱ ክፉ ምኞት ሲታለልና ሲሳብ ነው።
15ክፉ ምኞት ከተፀነሰ በኋላ ኀጢአት ይወለዳል፤ ኀጢአትም ካደገች በኋላ ሞት ይወለዳል።
16የተወደዳችሁ ወንድሞቼ አትታለሉ።
17ማንኛውም መልካምና ፍጹም ስጦታ እንደሚዘዋወር ጥላ ከማይለዋወጠው ከላይ ከሰማይ ከብርሃናት አባት ይወርዳል።
18በፍጥረታቱ መካከል እንደ በኵራት እንድንሆን እግዚአብሔር በእውነት ቃል ሕይወት ሊሰጠን ወደደ።
19የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ይህን ዕወቁ። ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገዬ፣ ለመቆጣትም የዘገዬ ይሁን!
20ምክንያቱም የሰው ቊጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያመጣም።
21ስለዚህ ርኵሰትንና በየቦታው ሞልቶ ያለውን ክፋት አስወግዳችሁ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁ የተተከለውን ቃል በትሕትና ተቀበሉ።
22ለቃሉ ታዘዙ እንጂ፣ ሰሚዎች ብቻ በመሆን ራሳችሁን አታታልሉ።
23ማንም ቃሉን እየሰማ ቃሉ የሚለውን ባያደርግ፣ ፊቱን በመስታወት እንደሚያይ ሰው ይሆናል።
24ፊቱን አይቶ ይሄዳል፤ ምን እንደሚመስል ግን ወዲያው ይረሳዋል።
25ፍጹሙንና ነጻ የሚያወጣውን ሕግ በጥንቃቄ የሚመለከትና የሚኖርበት እንጂ፣ ሰምቶ እንደሚረሳው ያልሆነ ሰው በሚያደርገው ሁሉ የተባረከ ይሆናል።
26አንድ ሰው ሃይማኖተኛ ነኝ እያለ፣ አንደበቱን ግን ባይቆጣጠር፣ ልቡን ያስታል፤ ሃይማኖቱም ከንቱ ነው።
27በእግዚአብሔር በአባታችን ፊት ንጹሕና ርኵሰት የሌለበት ሃይማኖት ይህ ነው፤ አባት የሌላቸውንና መበለቶችን በችግራቸው መርዳት፤ በዓለም ካለ ርኵሰት ራስን መጠበቅ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።