1ነገር ግን ተጨንቃ ለነበረች ጨለማ አይሆንም። በመጀመሪያው ዘመን የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር አቃለለ፣ በኋለኛው ዘመን ግን በዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ ያለውን የአሕዛብን ገሊላ ያከብራል።
2በጨለማ የሄደ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን በራላቸው።
3ሕዝቡን አብዝተሃል፣ ደስታንም ጨምረህላቸዋል፤ በመከር ደስ እንደሚላቸው፣ ሰዎችም ምርኮን ሲካፈሉ ደስ እንደሚላቸው በፊትህ ደስ ይላቸዋል።
4በምድያም ጊዜ እንደ ሆነ የሸክሙን ቀንበር የጫንቃውንም በትር የአስጨናቂውንም ዘንግ ሰብረሃል።
5የሚረግጡ የሰልፈኞች ጫማ ሁሉ፣ በደምም የተለወሰ ልብስ ለቃጠሎ ይሆናል፣ እንደ እሳት ማቃጠያም ሆኖ ይቃጠላል።
6ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።
7ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም። የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል።
8ጌታ በያዕቆብ ላይ ቃልን ሰደደ፣ በእስራኤልም ላይ ወደቀ።
9በትዕቢትና በልብ ኵራት የሚናገሩ በኤፍሬምና በሳርያ የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ።
10"ጡቡ ወድቆአል፣ ነገር ግን በተወቀረ ድንጋይ እንሠራለን፤ የሾላ ዛፎች ተቈርጠዋል፣ ነገር ግን ዝግባን እንተካባቸዋለን" የሚሉት ሁሉ ያውቃሉ።
11ስለዚህ እግዚአብሔር በረአሶን ላይ በጽዮን ተራራ ተቋቋሚ ያስነሣበታል፣
12ጠላቶቹን ሶርያውያንንም ከምሥራቅ፣ ፍልስጥኤማውያንንም ከምዕራብ ያንቀሳቅስበታል፤ እስራኤልንም በተከፈተ አፍ ይበሉታል። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፣ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።
13ሕዝቡ ግን ወደ ቀሠፋቸው አልተመለሱም፣ የሠራዊትንም ጌታ እግዚአብሔርን አልፈለጉም።
14ስለዚህ እግዚአብሔር ራስና ጅራትን፣ የሰሌኑን ቅርንጫፍና እንግጫውን በአንድ ቀን ከእስራኤል ይቆርጣል።
15ሽማግሌውና ከበርቴው እርሱ ራስ ነው፤ በሐሰትም የሚያስተምር ነቢይ እርሱ ጅራት ነው።
16ይህን ሕዝብ የሚመሩ ያስቱአቸዋል፤ በእነርሱ የሚመሩትም ይዋጣሉ።
17ስለዚህም ሰው ሁሉ ዝንጉና ክፉ ሠሪ ነውና፣ አፍም ሁሉ ስንፍናን ይናገራልና ስለዚህ ጌታ በጕልማሶቻቸው ደስ አይለውም፥ ለድሀ አደጎቻቸውና ለመበለቶቻቸውም አይራራም። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፣ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።
18ክፋት እንደ እሳት ይቃጠላል፤ ኵርንችቱንና እሾሁን ይበላል፤ ጭፍቅ የሆነውንም ዱር ያቃጥላል፥ ጢሱም ተትጐልጕሎ እንደ ዓምድ ይወጣል።
19በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ቍጣ ምድር ተቃጥላለች፤ ሕዝቡም እሳት እንደሚበላው እንጨት ሆኖአል፤ ሰውም ለወንድሙ ራርቶ አያድንም።
20ሰው ከቀኙ በኩል ሥጋ ቆርጦም ይራባል፤ ሥጋውን በግራ በኩል ይበላል አይጠግብምም። እያንዳንዱም የገዛ ራሱን ክንድ ሥጋ ይበላል፤
21ምናሴ ኤፍሬምን፣ ኤፍሬምም ምናሴን ይበላል፤ እነርሱም በአንድነት የይሁዳ ጠላቶች ይሆናሉ። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፣ ነገር ግን እጁ ገና ልትመታ ትዘረጋለች።