1እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፣ "ታላቅ ሰሌዳ ወስደህ፣ 'ምርኮ ፈጠነ፣ ብዝበዛ ቸኰለ' ብለህ ጻፍበት።
2የታመኑትን ሰዎች፣ ካህኑን ኦርዮንና የበራክዩን ልጅ ዘካርያስን ምስክሮች አድርግልኝ" አለኝ።
3ወደ ነቢይቱም ቀረብሁ፣ እርስዋም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች።
4ከዚያም እግዚአብሔር፣ "ሕፃኑ 'አባባ' እና 'እማማ' በማለት መጣራት ከማወቊ በፊት የደማስቆን ሀብትና የሰማርያን ምርኮ በአሦር ንጉሥ ፊት ይወስዳልና ስሙን ምርኮ ፈጠነ፣ ብዝበዛ ቸኰለ ብለህ ጥራው፤" አለኝ።
5እግዚአብሔር በድጋሚ ተናገረኝ፣ እንዲህም አለኝ፣
6"ይህ ሕዝብ በቀስታ የሚሄደውን የሰሊሆምን ውኃ ጠልቶአልና፣ ረአሶንንና የሮሜልዩንም ልጅ ወዶአልና፣
7ስለዚህ እግዚአብሔር ብርቱና ብዙ የሆነውን የወንዝ ውኃ፣ የአሦርን ንጉሥና ክብሩን ሁሉ፣ ያመጣባቸዋል። መስኖውንም ሁሉ ሞልቶ ይወጣል፣ በዳሩም ሁሉ ላይ ይፈስሳል፤
8እስከ አንገት እስኪደርስ ድረስ እየጐረፈ ወደ ይሁዳ ይገባል፣ እያጥለቀለቀም ያልፋል። አማኑኤል ሆይ፣ የክንፉ መዘርጋት የአገርህን ስፋት ትሞላለች።"
9አሕዛብ ሆ፣ እወቁና ደንግጡ፣ እናንተም አገራችሁ የራቀ ሁሉ፣ አድምጡ፤ ታጠቁም፣ ደንግጡ፤ ታጠቁ፤ ደንግጡ።
10ዕቅድን አብጁ፣ ነገር ግን አይከናወንም፤ ትእዛዙን ተናገሩ፣ ነገር ግን አይከናወንም፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና።
11እግዚአብሔር በጽኑ እጁ ጭምር እንዲህ ተናገረኝ፣ በዚህም ሕዝብ መንገድ አንዳልሄድ አስጠነቀቀኝ፣ እንዲህም አለኝ።
12ይህ ሕዝብ፣ አድማ ነው የሚሉትን ሁሉ፣ አድማ ነው አትበሉ፤ ማስፈራታቸውንም አትፍሩ፣ አትደንግጡ።
13ነገር ግን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን ቀድሱት፤ የሚያስፈራችሁና የሚያስደነግጣችሁም እርሱ ይሁን።
14እርሱም ለመቅደስ ይሆናል፤ ነገር ግን ለሁለቱ ለእስራኤል ቤቶች ለዕንቅፋት ድንጋይና ለማሰናከያ ዓለት ይሆናል። በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ለወጥመድና ለአሽክላ ይሆናል።
15ብዙዎችም በእርሱ ይሰናከላሉ፣ ይወድቁማል፣ ይሰበሩማል፣ ይጠመዱማል፣ ይያዙማል።
16ምስክሬን እሰር፣ በደቀ መዛሙርቶቼም መካከል ሕጉን አትም።
17ከያዕቆብም ቤት ፊቱን የሰወረውን እግዚአብሔርን እጠብቃለሁ፣ እጠብቀዋለሁም።
18ተመልከቱ፣ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ለእስራኤል በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክትና ተአምራት ነን።
19እነርሱ፣ "የሚጮኹትንና ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ጠይቁ" ባሉአችሁ ጊዜ፣ ሕዝቡ ከአምላኩ መጠየቅ አይገባውምን? ወይስ ለሕያዋን ሲሉ ሙታንን ይጠይቃሉን?
20ስለዚህ ለሕግና ለምስክር ትኩረት ልትሰጡ ይገባል! እንዲህም ያለውን ቃል ባይናገሩ፣ የንጋት ብርሃን ስለሌላቸው ነው።
21እነርሱም ተጨንቀውና ተርበው ያልፋሉ። በተራቡም ጊዜ፣ ተቈጥተው ንጉሣቸውንና አምላካቸውን ይረግማሉ፣ ፊታቸውን ወደ ላይያቀናሉ።
22ወደ ምድርም ይመለከታሉ፣ ተመልከቱ፣ መከራና ጨለማ፣ የሚያስጨንቅም ጭጋግ አለ። ወደ ድቅድቅም ጨለማ ይሰደዳሉ።