መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 10

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1መበለቶችም ቅሚያቸው እንዲሆኑ፣ ድሀ አደጎችንም ብዝበዛቸው እንዲያደርጉ፣ የድሀውን ፍርድ ያጣምሙ ዘንድ፣
2የችግረኛውንም ሕዝቤን ፍርድ ያጐድሉ ዘንድ የግፍን ትእዛዛት ለሚያዝዙ፣ ክፉንም ጽሕፈት ለሚጽፉ ወዮላቸው!
3በፍርድ ቀን፣ መከራም ከሩቅ በሚመጣበት ዘመን ምን ታደርጉ ይሆን? ለእርዳታስ ወደ ማን ትሸሻላችሁ? ብልጥግናችሁንስ ወዴት ትተዉታላችሁ?
4ከእስረኞች በታች ይጐነበሳሉ፣ ከተገደሉትም በታች ይወድቃሉ። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፣ ነገር ግን እጁ ገና ልትመታ ተዘርግታለች።
5ለቍጣዬ በትር ለሆነ፣ የመዓቴም ጨንገር በእጁ ላለ ለአሦር ወዮለት!
6እርሱንም በዝንጉ ሕዝብ ላይ እልካለሁ፣ ምርኮውንና ብዝበዛውንም ይወስድ ዘንድ እንደ አደባባይም ጭቃ የተረገጡ ያደርጋቸው ዘንድ በምቈጣቸው ሰዎች ላይ አዝዘዋለሁ።
7እርሱ እንዲሁ አያስብም፣ በዚህ ሁኔታ አይወጥንም። ነገር ግን በልቡ በርካታ አሕዛብን ለማጥፋትና ለመቍረጥ በልቡ አለ።
8እንዲህ ብላልና፣ "መሳፍንቴ ሁሉ ነገሥታት አይደሉምን?
9ካልኖ እንደ ከርከሚሽ አይደለችምን? ሐማትስ እንደ አርፋድ አይደለችምን? ሰማርያስ እንደ ደማስቆ አይደለችምን?
10የተቀረጹ ምስሎቻቸው ከኢየሩሳሌምና ከሰማርያ ምስሎች የበለጡትን የጣዖቶችን መንግሥታት እጄ እንደረታች፣
11በሰማርያና በጣዖቶችዋም እንዳደረግሁ፣ እንዲሁስ በኢየሩሳሌምና በጣዖቶችዋ አላደርግምን?"
12ስለዚህ እንዲህ ይሆናል፤ ጌታ ሥራውን ሁሉ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ በፈጸመ ጊዜ፣ "የአሦርን ንጉሥ የኩሩ ልብ ፍሬን የዓይኑንም ከፍታ ትምክሕት እቀጣለሁ።"
13እርሱ እንዲህ ብሎአልና፣ "አስተዋይ ነኝና በእጄ ኃይልና በጥበቤ አደረግሁት፤ የአሕዛብን ድንበሮች አራቅሁ፣ ሀብታቸውንም ዘረፍሁ፣ እንደ ጀግናም ሆኜ በምድር የተቀመጡትን አዋረድሁ፤
14እጄም የአሕዛብን ባለጠግነት እንደ ወፍ ቤት አገኘች፤ የተተወም እንቍላል እንደሚሰበሰብ፣ እንዲሁ እኔ ምድርን ሁሉ ሰበሰብሁ። ክንፉን የሚያራግብ አፉንም የሚከፍት የሚጮኽም የለም።"
15በውኑ መጥረቢያ በሚቈርጥበት ሰው ላይ ስለ ራሱ ይመካልን? ወይስ መጋዝ በሚስበው ላይ ራሱን ይክባልን? ይህስ፣ በትር የሚያነሣውን እንደ መነቅነቅ ዘንግም እንጨት ያይደለውን እንደ ማንሣት ያህል ነው።
16ስለዚህም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በወፍራሞች ጦረኞቹ ላይ ክሳትን ይልካል፤ ከክብሩም በታች ቃጠሎው እንደ እሳት መቃጠል ይነድዳል።
17የእስራኤልም ብርሃን እንደ እሳት፣ ቅዱሷም እንደ ነበልባል ይሆናል፤ እሾሁንና ኵርንችቱን በአንድ ቀን ያቃጥላል ይበላውማል።
18ከነፍስም እስከ ሥጋ ድረስ የዱሩንና የሚያፈራውን እርሻ ክብር ይበላል፣ ይህም የታመመ ሰው እንደሚሰለስል ይሆናል።
19ታናሽ ብላቴናም ይጽፋቸው ዘንድ እስኪችል ድረስ የቀሩት የዱር ዛፎች በቍጥር ጥቂት ይሆናሉ።
20በዚያም ቀን፣ የእስራኤል ቅሬታ ከያዕቆብም ቤት ያመለጡት ከእንግዲህ ወዲህ በመቱአቸው ላይ አይደገፉም፣ ነገር ግን በእስራኤል ቅዱስ በእግዚአብሔር ላይ በእውነት ይደገፋሉ።
21የያዕቆብም ቅሬታ ወደ ኃያል አምላክ ይመለሳሉ።
22እስራኤል ሆይ፣ የሕዝብህ ቍጥር እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆን ቅሬታው ይመለሳል። ጽድቅ የተትረፈረፈበትም ጥፋት ተወስኖአል።
23የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ያለቀ የተቈረጠ ጥፋትን በምድር ሁሉ መካከል ይፈጽማል።
24ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "በጽዮን የምትኖር ሕዝቤ ሆይ አሦርን አትፍራ። አሦር በበትር ይመታሃል፣ ግብጽም እንዳደረገ ዘንጉን ያነሣብሃል።
25ቍጣዬ እስኪፈጸም መዓቴም እስኪያጠፋቸው ድረስ በጣም ጥቂት ጊዜ ቀርቶአልና አትፍራው።"
26የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ምድያምን በሔሬብ ዓለት በኩል እንደ መታው ጅራፍ ያነሣበታል፤ በትሩንም በባሕር ላይ ያነሣል፣ በግብጽም እንዳደረገ ያነሣዋል።
27በዚያም ቀን፣ ሸክሙ ከጫንቃህ ቀንበሩም ከአንገትህ ላይ ይወርዳል፤ ቀንበሩም ከአንገትህ ከፍተኛ ውፍረት የተነሣ ይሰበራል።
28ጠላት ወደ አንጋይ መጥቶአል፤ በመጌዶን በኩል አልፎአል፤ በማክማስ ውስጥ ዕቃውን አኑሮአል፤
29በመተላለፊያ አልፎአል፤ በጌባ ማደሪያው ነው፤ ራማ ደንግጣለች፤ የሳኦል ጊብዓ ኰብልላለች።
30አንቺ የጋሊም ልጅ ሆይ፥ በታላቅ ድምፅሽ ጩኺ፤ ላይሳ ሆይ፥ አድምጪ! አንቺ ምስኪን ዓናቶት ሆይ፣ መልሽላት!
31መደቤና እየሸሸች ናት፣ በግቤርም የሚኖሩ ቤተሰቦቻቸውን አሽሽተዋል።
32ዛሬ በኖብ ይቆማል፤ በጽዮን ሴት ልጅ ተራራ በኢየሩሳሌም ኮረብታ ላይ ቡጢውን ይንጣል።
33ተመልከቱ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቅርንጫፎቹን በሚያስፈራ ኃይል ይቈርጣል፤ በቁመት የረዘሙትም ይቈረጣሉ፣ ከፍ ያሉትም ይዋረዳሉ።
34ጭፍቅ የሆነውንም ዱር በመጥረቢያ ይቈርጣል፣ ሊባኖስም በኃያሉ እጅ ይወድቃል።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።