መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 7

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ልጅ በኢዮአታም ልጅ በአካዝ ዘመን የሶርያ ንጉሥ ረአሶን፣ የእስራኤልም ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ፣ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፣ ሊያሸንፉአትም አልቻሉም።
2ለዳዊትም ቤት፣ ሶርያ ከኤፍሬም ጋር እንደተባበሩ ወሬ ተነገረ። የእርሱም ልብ፣ እንዲሁም የሕዝቡም ልብ፣ የዱር ዛፍ በነፋስ እንድትናወጥ ተናወጠ።
3ከዚያም እግዚአብሔር ኢሳይያስን፣ "አንተና ልጅህ ያሱብ አካዝን ትገናኙት ዘንድ በልብስ አጣቢው እርሻ መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኵሬ መስኖ ጫፍ ውጡ።
4እንዲህም በለው፣ 'ተጠንቀቅ፣ ዝምም በል፣ ስለ እነዚህ ስለሚጤሱ ስለ ሁለት የእንጨት ጠለሸቶች፣ ስለ ሶርያና ስለ ረአሶን፣ ስለ ሮሜልዩም ልጅ ቍጣ አትፍራ፣ ልብህም አይድከም።
5ሶርያና ኤፍሬም የሮሜልዩም ልጅ፣
6"ወደ ይሁዳ እንውጣ እናስጨንቃትም፣ እንስበራትም፣ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥባት" ብለው ክፋት ስለ መከሩብህ፤
7ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ይህ ምክር አይጸናምና አይሆንም፣
8የሶርያ ራስ ደማስቆ ስለሆነ፣ የደማስቆም ራስ ረአሶን ስለሆነ አይከናወንም። በስድሳ አምስት ዓመት ውስጥ ኤፍሬም ይሰባበራልና ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝብ አይሆንም፤
9የኤፍሬምም ራስ ሰማርያ ነው፣ የሰማርያም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው። በእምነት ባትጸኑ፣ በእርግጥም በዋስትና አትጸኑም።"
10እግዚአብሔርም ደግሞ አካዝን እንዲህ ብሎ ተናገረው፣
11"ከጥልቁ ወይም ከከፍታው ቢሆን ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ምልክትን ለምን።"
12አካዝ ግን፣ "አልለምንም፣ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም" አለ።
13ስለዚህ ኢሳይያስ ሲመልስ፣ "እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፣ ስሙ። በውኑ የሰውን ትእግሥት መፈታተናችሁ ቀላል ነውን? ዩአምላኬን ትእግሥት ደግሞ ልትፈታተኑ ይገባችኋልን?
14ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ ተመልከቱ፣ ድንግል ትፀንሳለች፣ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፣ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።
15ክፉን ለመጥላት መልካሙንም ለመምረጥ ሲያውቅ ቅቤና ማር ይበላል።
16ሕፃኑ ክፉን ለመጥላት መልካሙን ለመምረጥ ከማወቊ በፊት፣ የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት አገር ባድማ ትሆናለች።
17እግዚአብሔርም ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ ያልመጣውን ዘመን በአንተና በሕዝብህ በአባትህም ቤት ላይ ያመጣል፤ እርሱም የአሦር ንጉሥ መምጣት ነው።"
18በዚያም ጊዜ እግዚአብሔር በግብጽ ወንዝ ርቀት ያለውን ዝምብ፣ በአሦርም አገር ያለውን ንብ በፉጨት ይጠራል።
19ሁሉም ይመጡና በበረሃ ሸለቆ፣ በድንጋይም ዋሻ ውስጥ በእሾህ ቍጥቋጦ ሁሉ ላይ፣ በማሰማርያውም ሁሉ ላይ ይሰፍራሉ።
20በዚያም ቀን እግዚአብሔር ከወንዙ ማዶ በተከራየው ምላጭ በአሦር ንጉሥ የራሱንና የእግሩን ጠጕር ይላጨዋል፤ ምላጩም ጢሙን ደግሞ ይላጫል።
21በዚያም ቀን፣ ሰው አንዲት ጊደርንና ሁለት በጎችንም በሕይወት ያቆያል፣
22ደግሞም ከሚሰጡት ወተት ብዛት የተነሣ ቅቤ ይበላል፤ በአገሪቱም መካከል የቀረ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላል።
23በዚያም ቀን፣ ሺህ ብር የተገመተ ሺህ የወይን ግንድ በነበረበት ስፍራ ሁሉ ለኵርንችትና ለእሾህ ብቻ ይሆናል።
24ኵርንችትና እሾህ በምድር ሁሉ ላይ ነውና በፍላጻና በቀስት ወደዚያ ይገባሉ።
25በመቈፈርያም ወደ ተቈፈሩ ኮረብቶች ሁሉ ከኵርንችትና እሾህ ፍርሃት የተነሣ ወደዚያ አትሄድም፤ ነገር ግን የበሬ ማሰማርያና የበግ መራገጫ ይሆናል።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።