1የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል?
2በፊቱ እንደ ቡቃያ፣ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል። መልክና ውበት የለውም፣ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም።
3የተናቀ ከሰውም የተጠላ፣ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው። ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፣ እኛም አላከበርነውም።
4በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው።
5እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፣ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፣ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።
6እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ።
7ተጨቆነ፣ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፣ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።
8በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ?
9ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፣ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፣ በአፉም ተንኮል አልተገንበትም ነበር።
10እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፣ ዕድሜውም ይረዝማል፣ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል።
11ከነፍሱ መከራ በኋላ፣ ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፣ ኃጢአታቸውን ይሸከማል።
12ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፣ ከብዙ ኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፣ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፣ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።