መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 54

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1"አንቺ ያልወለድሽ መካን ሆይ፣ ዘምሪ፤ አንቺ ያላማጥሽ ሆይ፣ እልል በዪ፣ ጩኺም፤ ባል ካላት ይልቅ ፈት የሆነቺቱ ልጆች በዝተዋልና፣" ይላል እግዚአብሔር።
2የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፣ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ፤ አትቈጥቢ፤ አውታሮችሽን አስረዝሚ ካስሞችሽንም አጽኚ።
3በቀኝና በግራ ትሰፋፊያለሽና፣ ዘርሽም አሕዛብን ይወርሳልና፣ የፈረሱትንም ከተሞች መኖሪያ ያደርጋልና።
4አታፍሪምና አትፍሪ፤ አተዋረጂምና አትደንግጪ፤ የሕፃንነትሽንም እፍረት ትረሺዋለሽ፣ የመበለትነትሽንም ስድብ ከእንግዲህ ወዲህ አታስቢም።
5ፈጣሪሽ ባልሽ ነው፣ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ የእስራኤልም ቅዱስ ታዲጊሽ ነው፣ እርሱም የምድር ሁሉ አምላክ ይባላል።
6እግዚአብሔር እንደ ተተወችና እንደ ተበሳጨች በልጅነትዋም እንደ ተጣለች ሚስት ጠርቶሻል፣ ይላል አምላክሽ።
7"ለጥቂት ጊዜ ተውሁሽ፣ በታላቅም ምሕረት እሰበስብሻለሁ።
8በጥቂት ቍጣ ለቅጽበት ዓይን ፊቴን ከአንቺ ሰወርሁ፣ በዘላለምም ቸርነት እምርሻለሁ፣ ይላል ታዳጊሽ እግዚአብሔር።
9ይህ ለእኔ እንደ ኖኅ ውኃ ነው፤ የኖኅ ውኃ ደግሞ በምድር ላይ እንዳያልፍ እንደ ማልሁ፣ እንዲሁ አንቺን እንዳልቈጣ እንዳልገሥጽሽም ምያለሁ።
10ተራሮች ይፈልሳሉ፣ ኮረብቶችም ይወገዳሉ፤ ቸርነቴ ግን ከአንቺ ዘንድ አይፈልስም የሰላሜም ቃል ኪዳን አይወገድም፣ ይላል መሐሪሽ እግዚአብሔር።
11አንቺ የተቸገርሽ በዐውሎ ነፋስም የተናወጥሽ ያልተጽናናሽም፣ ተመልከቺ፣ ድንጋዮችሽን ሸላልሜ እገነባለሁ፣ በሰንፔርም እመሠርትሻለሁ።
12የግንብሽንም ጕልላት በቀይ ዕንቍ፣ በሮችሽንም በሚያብረቀርቅ ዕንቍ፣ ዳርቻሽንም ሁሉ በከበሩ ድንጋዮች እሠራለሁ።
13ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፣ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል።
14በጽድቅ ትታነጺያለሽ፤ ከግፍ ራቂ፣ አትፈሪምም፣ ድንጋጤም ወደ አንቺ አትቀርብም።
15ተመልከቺ፣ ይሰበሰባሉ፣ ነገር ግን ከእኔ ዘንድ አይሆንም፤ በአንቺም ላይ ችግር የሚፈጥሩ ሁሉ ይሸነፋሉ።
16ተመልከቺ፣ ፍሙን በወናፍ የሚያናፋ ለሥራውም መሣሪያ የሚያወጣ ብረት ሠሪን እኔ ፈጥሬአለሁ፤ የሚያፈርሰውንም እንዲያጠፋ ፈጥሬአለሁ።
17በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም፤ በፍርድም በሚነሣብሽ ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፣ ጽድቃቸውም ከእኔ ዘንድ ነው፣" ይላል እግዚአብሔር።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።