መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 5

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1አሁን ስለ ወዳጄና ስለ ወይን ቦታው ለወዳጄ ቅኔ እቀኛለሁ። ለወዳጄ በለመለመው ኮረብታ ላይ የወይን ቦታ ነበረው።
2በዙሪያው ቈፈረ፣ ድንጋዮችንም ለቅሞ አወጣ፣ ምርጥ የሆነውንም ወይን ተከለበት። በመካከሉም ግንብ ሠራ፣ ደግሞም የመጥመቂያ ጕድጓድ ማሰበት። ወይንንም ያፈራ ዘንድ ጠበቀ፣ ዳሩ ግን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ።
3ስለዚህ አሁን፣ እናንተ በኢየሩሳሌም የምትኖሩ የይሁዳ ሰዎች ሆይ፤ በእኔና በወይኑ ቦታዬ መካከል ፍረዱ።
4ለወይኔ ያላደረግሁለት፥ ከዚህ በተጨማሪ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድር ነው? መልካም ወይንን ያፈራል ብዬ ስትማመን፣ ስለ ምን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ?
5አሁንም በወይኔ ላይ የማደርገውን አስታውቃችኋለሁ፤ አጥሩን እነቅላለሁ፤ ለማሰማርያም ይሆናል፤ ቅጥሩንም አፈርሳለሁ፣ ለመራገጫም ይሆናል።
6ባድማ አደርገዋለሁ፤ አይቈረጥም፣ አይኰተኰትም፤ ኵርንችትና እሾህ ይበቅልበታል፤ ዝናብንም እንዳያዘንቡበት ዳመናዎችን አዝዛለሁ።
7የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ወይን ቦታ እርሱ የእስራኤል ቤት ነው፣ የደስታውም አትክልት የይሁዳ ሰዎች ናቸው፤ ፍርድን ይጠብቅ ነበር፣ እነሆም ግድያ ሆነ፤ ጽድቅንም ይተማመን ነበር፣ ይልቅ እርዳታ የሚለምን ጩኸት ሆነ።
8ስፍራ እስከማይቀር ድረስ እናንተም በምድር ላይ ብቻችሁን እስክትቀመጡ ድረስ፣ ቤትን ከቤት ጋር ለሚያያይዙ እርሻንም ከእርሻ ጋር ለሚያቀራርቡ ወዮላቸው!
9የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፣ ታላላቆቹና መልካም የሆኑት ቤቶች ሳይቀሩ ባድማ ይሆናሉ፣ የሚኖርባቸውም አይገኝም።
10ከወይኑ ቦታ ዐሥር ጥማድ በሬ ካረሰው አንድ የባዶስ መስፈሪያ ብቻ ይወጣል፤ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ዘር አንድ የኢፍ መስፈሪያ ብቻ ይሰጣል።
11ጠንካራ መጠጥን ለማፈላለግ በጠዋት ለሚነቊ፣ የወይን ጠጅም እስኪያቃጥላቸው እስከ ሌሊት ድረስ ለሚዘገዩ ወዮላቸው!
12መሰንቆና በገና፣ ከበሮና እምቢልታም፣ የወይን ጠጅም በግብዣቸው አለ፤ የእግዚአብሔርን ሥራ ግን አልተመለከቱም፣ እንዲሁም እጁ ያደረገችውን አላስተዋሉም።
13ስለዚህ ሕዝቤ ባለማወቃቸው ወደ ምርኮ ሄዱ፣ መሪዎቻቸውም ተራቡ፣ ሕዝባቸውም የሚጠጡት የላቸውም።
14ስለዚህም ሲኦል የመዋጥ ፍላጎትዋን አስፍታለች፣ አፍዋንም ያለ ልክ ከፍታለች፤ ከበርቴዎቻቸውና አዛውንቶቻቸው፣ ባለጠጎቻቸውም ደስተኞቻቸውም ወደ ሲዖል ይወርዳሉ።
15ሰውም ይጐሰቍላል፣ ሰውም ይዋረዳል፣ የትዕቢተኞችም ዓይን ትዋረዳለች።
16የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ግን በፍርድ ከፍ ከፍ ብሎአል፣ ቅዱሱም አምላክ በጽድቅ ተቀድሶአል።
17የበግ ጠቦቶች በገዛ መሰማርያቸው ውስጥ፣ እንዲሁም በባለጠጋ ሰዎች ጥፋት ውስጥ ይሰማራሉ፣ ጠቦቶችም ይግጣሉ።
18በደልን በምናምንቴ ገመድ፣ ኃጢአትንም በሰረገላ ማሰሪያ ወደ ራሳቸው ለሚስቡ፣ እናይ ዘንድ ይቸኵል፣
19"ሥራውንም ያፋጥን፤ እናውቃትም ዘንድ የእስራኤል ቅዱስ ምክር ትቅረብ፣ ትምጣ ለሚሉ ወዮላቸው!"
20ክፉውን መልካም፣ መልካሙን ክፉ ለሚሉ፤ ጨለማውን ብርሃን፣ ብርሃኑንም ጨለማ ለሚያደርጉ፤ ጣፋጩን መራራ፣ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!
21በገዛ ዓይናቸው ዘንድ ጥበበኞች፣ በነፍሳቸውም አስተዋዮች ለሆኑ ወዮላቸው!
22የወይን ጠጅ ለመጠጣት ኃያላን፣ የሚያሰክረውንም ብርቱ መጠጥ ለማደባለቅ ጨካኞች ለሆኑ፤
23በደለኛውን ስለ ጉቦ ጻድቅ ለሚያደርጉ፣ የጻድቁንም ጽድቅ ለሚያስወግዱበት ወዮላቸው!
24ስለዚህ የእሳት ወላፈን ቃርሚያን እንደሚበላ፣ እብቅም በነበልባል ውስጥ እንደሚጠፋ፣ እንዲሁ የእነርሱ ሥር የበሰበሰ ይሆናል፣ ቡቃያቸውም እንደ ትቢያ ይበንናል፣ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ሕግ ገፍተዋልና፣ የእስራኤልም ቅዱስ የተናገረውን ቃል አቃልለዋልና።
25ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነድዶአል፣ እጁንም በላያቸው ዘርግቶ ቀጥቷቸዋል፤ ተራሮችም ተንቀጠቀጡ፣ ሬሳቸውም በአደባባይ ላይ እንደ ጕድፍ ሆኖአል። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፣ ነገር ግን እጁ በድጋሚ ለመምታት ገና ተዘርግታለች።
26ለአሕዛብም በሩቅ ምልክትን ያቆማል፣ ከምድርም ዳርቻ በፉጨት ይጠራቸዋል። ተመልከቱ፣ እየተጣደፉ ፈጥነው ይመጣሉ።
27በመካከላቸው ደካማና ስንኵል የለባቸውም፣ የሚያንቀላፋና የሚተኛም የለም፤ የወገባቸውም መቀነት አይፈታም፣ የጫማቸውም ማሰሪያ አይበጠስም፤
28ፍላጾቻቸው ተስለዋል፣ ቀስቶቻቸውም ሁሉ ተለጥጠዋል፤ የፈረሶቻቸውም ኮቴ እንደ ቡላድ፣ የሰረገሎቻቸውም መንኰራኵር እንደ ዐውሎ ነፋስ ነው።
29ጩኸታቸው እንደ አንበሳ ነው፣ እንደ አንበሳ ደቦሎችም ያገሣሉ። ንጥቂያንም ይዘው ያገሣሉ፣ ይወስዱትማል፣ የሚታደግም የለም።
30በዚያም ቀን እንደ ባሕር መትመም ይተምሙባቸዋል፤ ወደ ምድርም ቢመለከቱ፣ ጨለማና መከራ ይመለከታል፤ ብርሃንም በደመናዎችዋ ውስጥ ጨልሞአል።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።