1አሁንም ባሪያዬ ያዕቆብ፣ የመረጥሁህም እስራኤል ሆይ፣ ስማ።
2የፈጠረህ፣ ከማኅፀንም የሠራህ፣ የሚረዳህም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ባሪያዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም ይሹሩን ሆይ፣ አትፍራ።
3በተጠማ ላይ ውኃን፣ በደረቅም መሬት ላይ ፈሳሾችን አፈስሳለሁና፤ መንፈሴን በዘርህ ላይ፣ በረከቴንም በልጆችህ ላይ አፈስሳለሁ፥
4በፈሳሾችም አጠገብ እንደሚበቅሉ እንደ አኻያ ዛፎች በሣር መካከል ይበቅላሉ።
5ይህ፣ 'እኔ የእግዚአብሔር ነኝ' ይላል፤ ሌላኛውም በያዕቆብ ስም ይጠራል፤ ይህም፣ 'እኔ የእግዚአብሔር ነኝ' ብሎ በእጁ ይጽፋል፣ በእስራኤልም ስም ይጠራል።"
6የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር የሚለው እንዲህ ነው - የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "እኔ ፊተኛ ነኝ፣ እኔም ኋለኛ ነኝ፣ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም።
7እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ይነሣና ይጥራ ይናገርም፤ ከጥንት የፈጠርሁትን ሕዝብ ያዘጋጅልኝ፣ የሚመጣውም ነገር ሳይደርስ ይንገሩኝ።
8አትፍሩ አትደንግጡም። ከጥንቱ ጀምሬ አልነገርኋችሁምን? ወይስ አላሳየኋችሁምን? እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፦ ከእኔ ሌላ አምላክ አለን? ሌላ ዐለት የለም፤ ማንንም አላውቅም።"
9የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩ ሁሉ ከንቱዎች ናቸው፤ የወደዱትም ነገር አይረባቸውም፤ ምስክሮቻቸውም አያዩምና አያውቁም፤ ስለዚህ እንዲያፍሩ ይደረጋሉ።
10አምላክን የሠራ ወይስ ለምንም የማይረባ ምስልን የቀረጸ ማን ነው?
11ተመልከቱ፣ ባልንጀሮቹ ሁሉ ያፍራሉ፤ ሠራተኞቹም ከሰዎች ወገን ብቻ ናቸው። ሁላቸው ተሰብስበው ይቁሙ፤ ይፈራሉ በአንድነትም ያፍራሉ።
12ብረት ሠሪ መጥረቢያውን ይሠራል፣ በፍምም ውስጥ ያደርገዋል፣ በመዶሻም መትቶ ቅርጽ ይሰጠዋል። በክንዱም ኃይል ይሠራዋል፣ እርሱም ይራባል፣ ይደክምማል፣ ውኃም አይጠጣም ይታክትማል።
13አናጢውም ገመድ ዘርግቶ በበረቅ ይለካዋል፣ በመቅረጫም ይቀርጸዋል። በመለኪያም ይለካዋል። በቤትም ውስጥ ይቀመጥ ዘንድ በሰው አምሳልና በሚስብ የሰው ውበት ያስመስለዋል።
14የዝግባን ዛፎች ይቈርጣል፣ የዞጲንና የኮምቦልን ዛፍ ይመርጣል። ከዱር ዛፎችም መካከል ይጠነክር ዘንድ ይተወዋል፤ የጥድንም ዛፍ ይተክላል ዝናብም ያበቅለዋል።
15ለሰውም ማገዶ ይሆናል፤ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፣ አዎን፣ አንድዶ እንጀራ ይጋግርበታል። ከእርሱም አምላክ አበጅቶ ይሰግድለታል፣ የተቀረጸውንም ምስል ሠርቶ በእርሱ ፊት ይንበረከካል።
16ግማሹን በእሳት ያቃጥላል፣ በዚያ በግማሹ ሥጋ ይበላል። ሥጋም ይጠብስበትና ይጠግባል። ራሱን ያሞቅና፣ "እሰይ ሞቅሁ፣ እሳቱን አይቻለሁ" ይላል።
17የቀረውንም እንጨት አምላክ አድርጎ ምስል ይቀርጽበታል፤ በፊቱም ተጐንብሶ ይሰግዳል ወደ እርሱም እየጸለየ፣ "አምላኬ ነህና፣ አድነኝ" ይላል።
18አያውቁም፣ አያስቡም፣ እንዳያዩ ዓይኖቻቸውን፣ እንዳያስተውሉ ልቦቻቸውን ታውረዋል።
19በልቡም ማንም አያስብም፣ "ግማሽዋን በእሳት አቃጥያለሁ፣ በፍምዋም ላይ እንጀራን ጋግሬአለሁ፣ ሥጋም ጠብሼ በልቻለሁ። የቀረውንም አስጸያፊ ነገር አደርጋለሁን? ለዛፍስ ግንድ እሰግዳለሁን? እንዲልም እውቀትና ማስተዋል የለውም።"
20አመድ ይበላል፤ የተታለለ ልብ አስቶታል። ነፍሱን ለማዳን አይችልም፣ ወይም፣ በቀኝ እጄ ሐሰት አለ" አይልም።
21ስለ እነዚህ ነገሮች አስብ፣ ያዕቆብ ሆይ፣ አንተም እስራኤል፣ ባሪያዬ ነህና ይህን አስብ፤ እኔ ሠርቼሃለሁ፤ አንተም ባሪያዬ ነህ፤ እስራኤል ሆይ፣ በእኔ ዘንድ ያልተረሳ ትሆናለህ።
22መተላለፍህን እንደ ደመና፣ ኃጢአትህንም እንደ ጭጋግ ደምስሼአለሁ፤ ተቤዥቼሃለሁና ወደ እኔ ተመለስ።
23ሰማያት ሆይ፣ እግዚአብሔር አድርጎታልና ዘምሩ፤ እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶአልና፣ በእስራኤልም ዘንድ ይከበራልና አንተ የምድር ጥልቅ ሆይ፣ ጩኽ፤ እናንተም ተራሮች፣ አንተም ዱር በአንተም ያለ ዛፍ ሁሉ፣ እልል በሉ።
24ከማኅፀን የሠራህ፣ የሚቤዥህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ሁሉን የፈጠርሁ፣ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ማን ነበረ?
25የሐሰተኞችን ምልክት ከንቱ አደርጋለሁ፣ ምዋርተኞችንም አሳብዳለሁ፣ ጥበበኞቹንም ወደ ኋላ እመልሳለሁ፣ እውቀታቸውንም ስንፍና አደርጋለሁ፤
26እኔ፣ እግዚአብሔር! የባሪያዬን ቃል አጸናለሁ፣ የመልእክተኞቼንም ምክር እፈጽማለሁ፤ ኢየሩሳሌምን፣ 'የሰው መኖሪያ ትሆኛለሽ፣' የይሁዳንም ከተሞች፣ 'ድጋሚ ትታነጻላችሁ፣ ፍራሾቻችሁንም አቆማለሁ' እላለሁ፤
27ቀላዩንም፣ 'ደረቅ ሁን፣ ፈሳሾችህንም አደርቃለሁ' እላለሁ፤
28ቂሮስንም፣ 'እርሱ እረኛዬ ነው፤ እርሱም ኢየሩሳሌምን፣ - 'ትታነጺያለሽ፣ ቤተ መቅደስም ይመሠረታል' ብሎ ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል" እላለሁ።