መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 45

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እግዚአብሔር ለቀባሁት፣ አሕዛብንም በፊቱ አስገዛ ዘንድ የነገሥታትንም ወገብ እፈታ ዘንድ፣ በሮቹም እንዳይዘጉ መዝጊያዎቹን በፊቱ እከፍት ዘንድ፣ ቀኝ እጁን ለያዝሁት ለቂሮስ እንዲህ ይላል፦
2"በፊትህ እሄዳለሁ ተራሮችንም ትክክል አደርጋለሁ፤ የናሱንም ደጆች እሰብራለሁ የብረቱንም መወርወሪያዎች እቈርጣለሁ፤
3በስምህም የምጠራህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ታውቅ ዘንድ፣ በጨለማ የነበረችውን መዝገብ በስውርም የተደበቀችውን ሀብት እሰጥሃለሁ።
4ስለ ባሪያዬ ስለ ያዕቆብ፣ ስለ መረጥሁትም ስለ እስራኤል ብዬ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ በቍልምጫ ስምህ ጠራሁህ፤ አንተ ግን አላወቅኸኝም።
5እኔ እግዚአብሔር ነኝ፣ ከእኔም ሌላ ማንም የለም፤ ከእኔም በቀር አምላክ የለም፤
6በፀሐይ መውጫና በምዕራብ ያሉ ከእኔ በቀር ማንም ሌላ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ አስታጠቅሁህ፥ አንተ ግን አላወቅኸኝም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፣ ከእኔም ሌላ ማንም የለም።
7ብርሃንን ሠራሁ፣ ጨለማውንም ፈጠርሁ፤ ደኅንነትን እሠራለሁ፣ ክፋትንም እፈጥራለሁ፤ እነዚህን ሁሉ ያደረግሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።
8እናንተ ሰማያት ከላይ አንጠባጥቡ፣ ደመናትም ጽድቅን ያዝንቡ! ምድርም ትከፈት መድኃኒትንም ታብቅል፣ ጽድቅም በአንድነት ይብቀል። እኔ እግዚአብሔር ፈጥሬዋለሁ።
9ከሠሪው ጋር ለሚከራከር ወዮለት! በምድር ሸክላዎች መካከል ያለ ሸክላ ነው! ጭቃ የሚሠራውን፣ 'ምን ትሠራለህ?' ወይስ 'ሥራህ - እጅ የለውም' ይላልን?
10አባቱን፣ 'ምን ወልደሃል?' ወይም ሴትን፣ 'ምን አማጥሽ?' ለሚል ወዮ!
11የእስራኤል ቅዱስ፣ ሠሪውም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'ስለሚመጣው ነገር ጠይቁኝ፣ ስለ ልጆቼና ስለ እጄ ሥራም እዘዙኝ።'
12'እኔ ምድርን ሠርቻለሁ ሰውንም በእርስዋ ላይ ፈጥሬአለሁ። እኔ በእጄ ሰማያትን ዘርግቼአለሁ፣ ሠራዊታቸውንም ሁሉ አዝዣለሁ።
13እኔ ቂሮስን በጽድቅ አስነሥቼዋለሁ፣ መንገዱንም ሁሉ አቀናለሁ። እርሱ ከተማዬን ይገነባል፣ በዋጋም ወይም በደመወዝ ሳይሆን ምርኮኞቼን ያወጣል፣" ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
14እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፣ "የግብጽ ድካምና የኢትዮጵያ ንግድ ቁመተ ረጅሞችም የሳባ ሰዎች ወደ አንተ ያልፋሉ፤ ለአንተም ይሆናሉ። እጆቻቸውም ታስረው ይከተሉሃል፤ በፊትህም ያልፋሉ፣ ለአንተም እየሰገዱ። 'በእውነት እግዚአብሔር በአንተ አለ፣ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም' ብለው ይለምኑሃል።"
15የእስራኤል አምላክ መድኃኒት ሆይ፣ በእውነት አንተ ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ።
16ሁሉም ያፍራሉ ይዋረዱማል፤ ጣዖታትንም የሚሠሩ በአንድነት ወደ ውርደት ይሄዳሉ።
17እግዚአብሔር ግን እስራኤልን በዘላለማዊ መድኃኒት ያድነዋል፤ እናንተም ለዘላለም አታፍሩምና አትዋረዱም።
18ሰማያትን የፈጠረ እግዚአብሔር፣ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፣ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ፣ እንዲህ ይላል፣ "እኔ እግዚአብሔር ነኝ፣ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።
19በስውር ወይም በጨለማ ምድር ስፍራ አልተናገርሁም፤ ለያዕቆብ ዘር፣ 'በከንቱ ፈልጉኝ አላልሁም!' እኔ እግዚአብሔር ጽድቅን እናገራለሁ፣ ቅንንም አወራለሁ።
20እናንተ ከአሕዛብ ወገን ሆናችሁ ያመለጣችሁ ኑ! ተሰብስባችሁ ኑ፣ በአንድነትም ቅረቡ! የተቀረጸውን የምስላቸውን እንጨት የሚሸከሙና ያድን ዘንድ ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ እውቀት የላቸውም።
21ይናገሩ ይቅረቡም በአንድነትም ይማከሩ! ከጥንቱ ይህን ያሳየ ከቀድሞስ የተናገረ ማን ነው? ያሳየሁም የተናገርሁም እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ ጻድቅ አምላክና መድኃኒት ነኝ፣ ከእኔም በቀር ማንም የለም።
22እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፣ እኔ አምላክ ነኝና፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ።
23'ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፣ አትመለስም። ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፣ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ።
24ስለ እኔም፣ "በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ጽድቅና ኃይል አለ፣ ወደ እርሱም ሰዎች ይመጣሉ።" በእርሱም ላይ የተቈጡ ሁሉ ያፍራሉ።
25የእስራኤልም ዘር ሁሉ በእግዚአብሔር ይጸድቃሉ፤ ይመካሉም ይባላል።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።