መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 43

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1አሁንም ያዕቆብ ሆይ፣ የፈጠረህ፣ እስራኤልም ሆይ፣ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፣ አንተ የእኔ ነህ።
2በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፣ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፥ ነበልባሉም አይፈጅህም።
3እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኃኒትህ ነኝ፤ ግብጽን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፣ ኢትዮጵያንና ሳባንም ለአንተ ፋንታ ሰጥቻለሁ።
4በዓይኔ ፊት የከበርህና የተመሰገንህ ነህና፣ እኔም ወድጄሃለሁና ስለዚህ ሰዎችን ለአንተ አሕዛብንም ለነፍስህ እሰጣለሁ።
5እኔ ከአንተ ጋር ነኝና፣ አትፍራ፤ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፣ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ።
6ሰሜንን፣ 'መልሰህ አምጣ፣' ደቡብንም፣ 'ማናቸውንም አትከልክል፤' ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ፣ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፣
7በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፣ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ።
8ዓይኖች ያሉአቸውን ዕውሮችን ሕዝብ፣ ጆሮችም ያሉአቸውን ደንቆሮቹን አውጣ።
9አሕዛብ ሁሉ በአንድነት ይሰብሰቡ፣ ወገኖችም ይከማቹ። ከመካከላቸው፤ ይህን የሚናገር፣ የቀድሞዎቹንስ ክስተቶች የሚያሳየን ማን ነው? ይጸድቁ ዘንድ ምስክሮቻቸውን ያምጡ፣ ሰምተውም 'እውነት ነው' ይበሉ።
10"ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ፣ እኔም እንደሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፣ እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ" ይላል እግዚአብሔር። ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም።
11እኔ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፣ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም።
12ተናግሬአለሁ፣ አድኜማለሁ፣ አውጄማለሁ፥ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምላክ አልነበረም። ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፣" ይላል እግዚአብሔር። "እኔም አምላክ ነኝ።"
13ከጥንት ጀምሮ እኔ ነኝ፣ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፤ እሠራለሁ፣ የሚከለክልስ ማን ነው?"
14የእስራኤል ቅዱስ፣ የሚቤዣችሁ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ "ስለ እናንተ ወደ ባቢሎን ሰድጃለሁ፣ ከለዳውያንንም ሁሉ ስደተኞች አድርጌ በሚመኩባቸው መርከቦች አዋርዳቸዋለሁ።
15ቅዱሳችሁ፣ የእስራኤል ፈጣሪ፣ ንጉሣችሁ፣ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።"
16እግዚአብሔር የሚለው ይህንን ነው (በባሕር ውስጥ መንገድን በኃይለኛም ውኃ ውስጥ መተላለፊያን ያደርጋል፤
17እግዚአብሔር ሠረገላውንና ፈረሱን፣ ሠራዊቱንና አርበኛውን ያወጣል። እነርሱ ግን በአንድነት ተኝተዋል፤ መቼም አይነሡም፤ ቀርተዋል፣ እንደ ጥዋፍ ኩስታሪም ጠፍተዋል።)
18"የፊተኛውን ነገር አታስተውሉ፣ የጥንቱንም ነገር አታስቡ።
19ተመልከቱ፣ አዲስ ነገርን አደርጋለሁ፤ እርሱም አሁን ይበቅላል፣ አታዩትምን? በምድረ በዳም መንገድን በበረሀም ወንዞችን አደርጋለሁ።
20የምድረ በዳ አራዊት፥ ቀበሮችና ሰጎኖች፥ ያከብሩኛል።
21ምስጋናዬን እንዲናገሩ ለእኔ የፈጠርሁት ሕዝብ፣ የመረጥሁትን ሕዝቤን አጠጣ ዘንድ በምድረ በዳ ውኃን በበረሀም ወንዞችን ሰጥቻለሁና።
22ያዕቆብ ሆይ፣ አንተ ግን አልጠራኸኝም፣ አንተም እስራኤል ሆይ፣ በእኔ ዘንድ ደክመሃል።
23ለሚቃጠል መሥዋዕት በጎችህን አላቀረብህልኝም፣ በሌላም መሥዋዕትህ አላከበርኸኝም፤ በእህልም ቍርባን አላስቸገርሁህም፣ በዕጣንም አላደከምሁህም።
24ጣፋጭ መዐዛ ያለው ዕጣን በገንዘብ አልገዛህልኝም፣ በመሥዋዕትህም ስብ አላጠገብኸኝም፤ ነገር ግን በኃጢአትህ አስቸገርኸኝ፣ በበደልህም አደከምኸኝ።
25አዎን፣ መተላለፍህን፣ ስለ እኔ ስል የምደመስስ እኔ ነኝ፤ ኃጢአትህንም ከእንግዲህ አላስብም።
26የተከሰተውን አሳስበኝ። በአንድነትም ሆነን እንከራከር፤ ስለ ንጹህነትህ እንድትጸድቅ ነገርህን ተናገር።
27የመጀመሪያው አባትህ ኃጢአት ሠርቶአል፣ መምህሮችህም በድለውኛል።
28ስለዚህ የመቅደሱን ቅዱሳን አለቆች አረከስሁ፣ ያዕቆብንም እርግማን፣ እስራኤልንም ስድብ አደረግሁ።"
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።