መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 33

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1አንተ ሳትጠፋ የምታጠፋ፣ በአንተም ላይ ወንጀል ሳይደረግ ወንጀል የምታደርግ ወዮልህ! ማጥፋትን በተውህ ጊዜ ትጠፋለህ፣ አሳልፎ መስጠትንም በተውህ ጊዜ አሳልፈው ይሰጡሃል።
2እግዚአብሔር፣ ማረን፤ አንተን ተማምነናል፤ በየጠዋቱ ክንድ፣ በመከራም ጊዜ ማዳን ሁነን።
3ከታላቅ ጫጫታ ወገኖች ሸሹ፣ ስትነሣም አሕዛብ ተበትነዋል።
4አንበጣ እንደሚሰበስብ፣ ምርኮአችሁ ትሰበሰባለች፣ ኩብኩባም እንደሚዘልል፣ ሰዎች ይዘልሉበታል።
5እግዚአብሔር ገነነ። እርሱ በአርያም ይኖራል። ጽዮንን በፍትህና በጽድቅ ሞላት።
6የዘመንህም ጸጥታ፣ የመድኃኒት ብዛት፣ ጥበብና እውቀት ይሆናል፤ እግዚአብሔርን መፍራት መዝገቡ ነው።
7ተመልከቱ፣ ባለሥልጣናቶቻቸው በጎዳና ይጮኻሉ፤ የሰላም መልእክተኞች መራራ ለቅሶ ያለቅሳሉ።
8መንገዶች ተራቆቱ፣ ተላላፊም ቀረ፤ እርሱም ቃል ኪዳንን አፈረሰ፣ ከተሞችንም ናቀ ሰውንም አልተመለከተም።
9ምድሪቱ አለቀሰች ከሳችም፤ ሊባኖስ አፈረ ጠወለገም፤ ሳሮን እንደ ምድረ በዳ ሆነ፤ ባሳንና ቀርሜሎስ ቅጠላቸውን አረገፉ።
10"አሁን እነሣለሁ" ይላል እግዚአብሔር፤ "አሁን እከበራለሁ፤ አሁን ከፍ ከፍ እላለሁ።"
11ገለባን ትፀንሳላችሁ፣ እብቅንም ትወልዳላችሁ፤ እስትንፋሳችሁ የምትበላችሁ እሳት ናት።
12አሕዛብም እንደ ተቃጠለ ኖራ፣ ተቈርጦም በእሳት እንደ ተቃጠለ እሾህ ይሆናሉ።
13እናንተ በሩቅ ያላችሁ፣ የሠራሁትን ስሙ፣ እናንተም በቅርብ ያላችሁ ኃይሌን እወቁ።"
14በጽዮን ያሉ ኃጢአተኞች ፈሩ፣ መንቀጥቀጥ ዝንጉዎቹን ያዘ፤ ከምትበላ እሳት ጋር መኖርን የሚችል ከእኛ ማን አለ? ለዘላለምም ከምትነድድ እሳት ጋር መኖርን የሚችል ከእኛ ማን አለ?
15በጽድቅ የሚሄድ ቅን ነገርንም የሚናገር፤ በሽንገላ የሚገኝ ትርፍን የሚንቅ፥ መማለጃ ጉቦን ከመጨበጥ እጁን የሚያርቅ፣ ደም የማፍሰስ ወንጀልን ከመስማት ጆሮቹን የሚያደነቍር፣ ክፋትንም ከማየት ዓይኖቹን የሚጨፍን ነው።
16እርሱ ከፍ ባለ ስፍራ ይቀመጣል፣ ጠንካራ አምባ መጠጊያው ይሆናል፣ እንጀራም ይሰጠዋል፣ ውኃውም የታመነች ትሆናለች።
17ዓይኖችህ ንጉሥን በውበቱ ያዩታል፤ እነርሱም በሩቅ ያለች ሰፊ ምድርን ያዩአታል።
18ልብህም፣ ጸሐፊ ወዴት አለ? ገንዘቡንስ መዛኝ ወዴት አለ? ግንቦቹንስ የቈጠረ ወዴት አለ? ብሎ የሚያስፈራ ነገር ያስባል።
19ጨካኝን ሕዝብ፣ ቋንቋው ለማስተዋል ጥልቅ የሆነውንና አንደበቱ ለማስተዋል ጸያፍ የሆነውን ሕዝብ፣ አታይም።
20የበዓላችንን ከተማ ጽዮንን ተመልከት፣ ዓይኖችህ የሰላም ማደሪያ፣ ካስማውም ለዘላለም የማይነቀል፣ አውታሩም ሁሉ የማይበጠስ፣ የማይወገድ ድንኳን የሆነውን ኢየሩሳሌምን ያያሉ።
21ይልቅ፣ እግዚአብሔር በዚያ የሰፉ ወንዞችና የመስኖች ስፍራ ሆኖ ከእኛ ጋር በግርማ ይሆናል። የሚቀዘፉ መርከቦች አይጓዙባትም፣ ታላላቆችም መርከቦች አያልፉባትም።
22እግዚአብሔር ፈራጃችን ነውና፣ እግዚአብሔር ሕግን የሰጠን ነውና፣ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው፤ እርሱ ያድነናል።
23ገመዶችህ ላልተዋል፣ ደቀላቸውንም አላጸኑም፣ ሸራውንም መዘርጋት አልቻሉም፤ በዚያም ጊዜ የብዙ ምርኮ ብዝበዛ ተከፈለ፤ አንካሶች እንኳ ብዝበዛውን በዘበዙ።
24በዚያም የሚኖር፣ "ታምሜአለሁ፣" አይልም፤ በእርስዋም ለሚቀመጡ ሰዎች በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።