1እናንተ አሕዛብ ሆይ፣ ቅረቡ፣ ስሙ፤ እናንተ ሕዝቦች ሆይ፣ አድምጡ! ምድርና ሞላዋ፣ ዓለምና ከእርስዋ የሚወጣ ሁሉ ይስሙ።
2የእግዚአብሔር ቍጣ በአሕዛብ ሁሉ ላይ፣ መዓቱም በሠራዊታቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ፈጽሞ አጠፋቸው፣ ለመታረድም አሳልፎ ሰጣቸው።
3ከእነርሱም የተገደሉት ይጣላሉ፣ የሬሳቸውም ግማት በሁሉ ቦታ ይሸታል፣ ተራሮችም በደማቸው ይርሳሉ።
4የሰማይም ሠራዊት ሁሉ ይበሰብሳሉ፣ ሰማያትም እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ይጠቀለላሉ፣ ከወይንና ከበለስም ቅጠል እንደሚረግፍ፣ ሠራዊታቸው ሁሉ ይረግፋል።
5ሰይፌ በሰማይ ሆና እስክትረካ ድረስ ጠጥታለች፤ ተመልከቱ፣ በኤዶምያስና በረገምሁት ሕዝብ ላይ አሁን ለፍርድ ትወርዳለች።
6የእግዚአብሔር ሰይፍ በደም ተሞልታለች፣ በስብም፣ በበግ ጠቦትና በፍየል ደምም፣ በአውራም በግ ኵላሊት ስብ ወፍራለች። እግዚአብሔር መሥዋዕት በባሶራ፣ ታላቅም እርድ በኤዶምያስ ምድር አለውና።
7ጎሽ ከእነርሱ ጋር፣ ወይፈኖችም ከኮርማዎች ጋር ይወድቃሉ፤ ምድራቸውም በደም ትረካለች፣ አፈራቸውም በስብ ትወፍራለች።
8የእግዚአብሔር የበቀሉ ቀን፣ ስለ ጽዮንም ክርክር የብድራት ዓመት ነው።
9የኤዶምያስም ምንጮች ዝፍት ሆነው ይለወጣሉ፣ አፈርዋም ዲን ይሆናል፣ መሬትዋም የሚቀጠል ዝፍት ትሆናለች።
10በሌሊትና በቀንም ይቃጠላል፣ ጢስዋም ለዘላለም ይወጣል፤ ከትውልድ እስከ ትውልድም ድረስ ባድማ ሆና ትኖራለች፤ ለዘላለም ዓለም ማንም አያልፍባትም።
11ነገር ግን፣ ጭልፊትና ጃርት ግን ይኖሩባታል፤ ጕጕትና ቍራም መረባቸውን ይሠሩባታል። በላይዋም የመፍረስ ገመድና የባዶነት ቱንቢ ይዘረጋባታል።
12መሳፍንቶችዋን ወደ መንግሥት ይጠራሉ፣ ነገር ግን ማንም አይገኝባትም፤ አለቆችዋም ሁሉ ምናምኖች ይሆናሉ።
13በቤተ መንግሥቶቿ እሾህ፣ በቅጥሮችዋም ሳማን፣ አሜከላ ይበቅሉባታል፤ የቀበሮም ማደሪያና የሰጐን ስፍራ ትሆናለች።
14የምድረ በዳም አራዊት ከተኵሎች ጋር ይገናኛሉ፣ አጋንንትም እርስ በርሳቸው በጩኸት ይጠራራሉ፤ ጅንም በዚያ ትኖራለች ለእርስዋም ማረፊያ ታገኛለች።
15በዚያም ዋሊያ ቤትዋን ትሠራለች፣ እንቍላልም ትጥላለች ትቀፈቅፈውማለች ልጆችዋንም በጥላዋ ትሰበስባለች፤ በዚያም ደግሞ አሞራዎች እያንዳንዳቸው ከባልንጀሮቻቸው ጋር ይሰበሰባሉ።
16በእግዚአብሔር የመጽሐፍ ጥቅልል ውስጥ ፈልጉ፣ አንዳቸውም አይጠፉም። አፌ አዝዞአልና፣ መንፈሱም ሰብስቦአቸዋልና ከእነዚህ አንዲት አትጠፋም፣ ባልንጀራውንም የሚያጣ የለም።
17እርሱም ዕጣ ጣለባቸው፣ እጁም በገመድ ከፈለችላቸው፤ ለዘላለም ይገዙአታል፣ ከትውልድም እስከ ትውልድ ድረስ ይቀመጡባታል።