መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 32

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ተመልከቱ፣ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል፣ መሳፍንትም በፍርድ ይገዛሉ።
2ሰውም ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ፣ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሃም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ ይሆናል።
3ከዚያም፣ የሚያዩትም ሰዎች ዓይኖች አይደበዝዙም፣ የሚሰሙትም ጆሮች በትኩረት ያደምጣሉ።
4ጥንቃቄ የሌላቸው ሰዎች ልብ እውቀትን ታስተውላለች፣ የተብታቦችም ምላስ በቀላሉ አድርጋ ትናገራለች።
5ከእንግዲህ ወዲህ ሰነፍ ከበርቴ ተብሎ አይጠራም፣ አታላዩም የተገራ አይባልም።
6ሰነፍ ግን ስንፍናን ይናገራል፣ ልቡም ዝንጉነትን ይፈጽም ዘንድ በእግዚአብሔርም ላይ ስሕተትን ይናገር ዘንድ፣ የተራበችውንም ሰውነት ባዶ ያደርግ ዘንድ፣ ከተጠማም ሰው መጠጥን ይቈርጥ ዘንድ በደልን ይሠራል።
7የንፉግም ዕቃ ክፉ ናት። ችግረኛ ትክክል ነገርን በተናገረ ጊዜ እንኳ እርሱ በሐሰት ቃል ድሀውን ያጠፋ ዘንድ ክፉን አሳብ ያስባል።
8ነገር ግን፣ ከበርቴው ሰው ለመከበር ያስባል፤ በመከበርም ጸንቶ ይኖራል።
9እናንተ ዓለመኞች ሴቶች ሆይ፣ ተነሡ፣ ድምፄንም ስሙ፤ እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴቶች ልጆች ሆይ፣ ንግግሬን አድምጡ።
10እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴቶች ሆይ፣ ወይንን መሰብሰብ ይቀራልና፣ ፍሬም ማከማቸት አይመጣምና ከዓመትና ከጥቂት ቀን በኋላ ትንቀጠቀጣላችሁ።
11እናንተ ዓለመኞች ሴቶች ሆይ፣ ተጠንቀቁ፤ ተማምናችሁም የምትቀመጡ ሆይ፣ ተንቀጥቀጡ፤ የቅምጥል ልብሳችሁን አውልቁ፣ ዕራቁታችሁን ሁኑ፣ ወገባችሁንም በማቅ ታጠቁ።
12ስለ ተወደደችውም እርሻ፣ ስለሚያፈራውም ወይን ደረታችሁን ድቁ።
13በሕዝቤ ምድር ላይ፣ በደስታ ከተማ ባሉት በደስታ ቤቶች ሁሉ ላይ እሾህና ኵርንችት ይወጣባቸዋል፤
14አዳራሹ ወና ትሆናለችና፣ የብዙ ሰውም ከተማ ትለቅቃለችና፣ አምባውና ግንቡም ለዘላለም ዋሻ፣ የምድረ በዳም አህያ ደስታ፣ የመንጎችም ማሰማርያ ይሆናልና፤
15ይህም፣ መንፈስ ከላይ እስኪፈስስልን፣ ምድረ በዳውም ፍሬያማ እርሻ እስኪሆን፣ ፍሬያማውም እርሻ ጫካ ተብሎ እስኪቈጠር ድረስ ይሆናል።
16ከዚያ በኋላ ፍርድ በምድረ በዳ ይኖራል፤ ጽድቅም በፍሬያማው እርሻ ያድራል።
17የጽድቅም ሥራ ሰላም፣ የጽድቅም ፍሬ ለዘላለም ጸጥታና መታመን ይሆናል።
18ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ፣ በታመነም ቤት በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል።
19በረዶ ግን በዱር ላይ ይወርዳል፣ ከተማም ፈጽማ ትዋረዳለች፣
20እናንተ የበሬና የአህያ እግር እየነዳችሁ በውኃ ሁሉ አጠገብ የምትዘሩ ትባረካላችሁ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።