1"ለዓመፀኞች ልጆች ወዮላቸው፣" ይላል እግዚአብሔር። "ከእኔ ዘንድ ያልሆነን ዕቅድ ይመክራሉ፣ ኃጢአትንም በኃጢአት ላይ ይጨምሩ ዘንድ በመንፈሴ ያልተመራውን የትብብር ኪዳን ያደርጋሉ።
2ከእኔም ምሪትን ሳይጠይቁ ወደ ግብጽ ይሄዱ ዘንድ ይወጣሉ። በፈርዖን ኃይል ይጸኑ ዘንድ በግብጽም ጥላ ይታመኑ ዘንድ ይፈልጋሉ።
3ስለዚህ የፈርዖን ከለላ እፍረት፣ በግብጽም ጥላ መታመን ውርደት ይሆንባችኋል።
4አለቆቻቸው በጣኔዎስ ቢሆኑ እንኳን፣ መልክተኞቻቸውም ወደ ሓኔስ ቢደርሱ እንኳን።
5ሁላቸው ይጠቅሙአቸው ዘንድ ስለማይችሉ፣ እፍረትና ስድብ እንጂ ረድኤትና ረብ ስለማይሆኑ ሕዝብ ያፍራሉ።
6በኔጌቭ ስላሉ አውሬዎች የተነገረ ሸክም፦ ተባትና እንስት አንበሳ እፉኝትም ነዘር እባብም በሚወጡባት በመከራና በጭንቀት ምድር በኩል ብልጥግናቸውን በአህዮች ጫንቃ ላይ መዛግብቶቻቸውንም በግመሎች ሻኛ ላይ እየጫኑ ወደማይጠቅሙአቸው ሕዝብ ይሄዳሉ።
7የግብጽ እርዳታ ከንቱና ምናምን ነው፤ ስለዚህ ስሙን፣ ተረጋግጦ የሚቀመጥ ረዓብ ብዬ ጠርቼዋለሁ።
8አሁንም ሂድ፣ ለሚመጣውም ዘመን ለምስክርነት እንዲሆን በሰሌዳ ላይ በመጽሐፍም ውስጥ ጻፍላቸው።
9እነዚህ ዓመፀኛ ሕዝብ ናቸውና፣ የእግዚአብሔርን ሕግ ለመስማት የማይወድዱ የሐሰት ልጆች ናቸውና።
10ለባለ ራእዮች፣ "አትመልከቱ፤" ይላሉ፣ ለነቢያትም፣ "የለዘበውን ነገር፣ አታላዩን ነገር እንጂ፣ ቀጥተኛውን እውነት አትንገሩን፤
11ከመንገድ ፈቀቅ በሉ፤ ከጐዳናውም ዘወር በሉ፤ የእስራኤልንም ቅዱስ ከእኛ ዘንድ አስወግዱ" ይሉአቸዋል።
12ስለዚህ የእስራኤል ቅዱስ እንዲህ ይላል፣ "ይህችን ቃል አቃልላችሁ፣ በግፍና በጠማምነት ታምናችኋልና፣ በእርሱም ተደግፋችኋልና፣
13ስለዚህ ይህ በደል አዘብዝቦ ለመፍረስ እንደ ቀረበ፣ አፈራረሱም ፈጥኖ ድንገት እንደሚመጣ እንደ ረጅም ቅጥር ይሆንባችኋል።"
14የሸክላ ሠሪ ማድጋ እንደሚሰበር ይሰብረዋል፤ ሳይራራም ያደቅቀዋል፤ ከስባሪውም እሳት ከማንደጃ የሚወስዱበት ወይም ውኃ ከጕድጓድ የሚቀዱበት ገል አይገኝም።
15የእስራኤል ቅዱስ፣ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፣ "በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል። እናንተም እንቢ አላችሁ።
16ነገር ግን፣ 'አይሆንም፣ በፈረስ ላይ ተቀምጠን እንሸሻለን እንጂ እንዲህ አይሆንም' አላችሁ፣ ስለዚህም ትሸሻላችሁ፤ ደግሞም፣ 'በፈጣን ፈረስ ላይ እንቀመጣለን' አላችሁ፣ ስለዚህም የሚያሳድዱአችሁ ፈጣኖች ይሆናሉ።
17ከአንድ ሰው ዛቻ የተነሣ ሺህ ሰዎች ይሸሻሉ፤ እናንተም በተራራ ራስ ላይ እንዳለ ምሰሶ፣ በኮረብታም ላይ እንዳለ ምልክት ሆናችሁ እስክትቀሩ ድረስ፣ ከአምስት ሰዎች ዛቻ የተነሣ ትሸሻላችሁ።"
18ይሁን እንጂ እግዚአብሔርም የፍርድ አምላክ ነውና ስለዚህ እግዚአብሔር ይራራላችሁ ዘንድ ይታገሣል፣ ይምራችሁም ዘንድ ከፍ ከፍ ይላል፤ እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁ ሁሉ ብሩካን ናቸው።
19በኢየሩሳሌም ውስጥ በጽዮን የምትኖሩ ሕዝብ ሆይ፣ ከእንግዲህ ወዲህ አታለቅሱም፤ በጩኸትም ድምፅ ይራራላችኋል፣ በሰማችሁም ጊዜ ይመልስላችኋል።
20ጌታም የጭንቀትን እንጀራና የመከራን ውኃ ቢሰጥህም፣ አስተማሪህ ከእንግዲህ ከአንተ አይሰወርም፣ ነገር ግን አስተማሪህን በገዛ ራስህ ዐይኖች ታያለህ።
21ወደ ቀኝም ወደ ግራም ብትዞር ከበስተኋላህ ጆሮችህ "መንገዱ ይህች ናት፣ በእርስዋም ሂድ" የሚለውን ቃል ይሰማሉ።
22በብርም የተለበጡትን የተቀረጹትን ምስሎችህን በወርቅም የተለበጡትን ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎችህን ታረክሳለህ፤ እንደ ርኩስ ጨርቅ ትጥላቸዋለህ። "ከዚህ ውጡ" ትላቸውማለህ።
23በምድርም ለተዘራው ዘርህ ዝናብ ይሰጣል፣ ከምድርም ፍሬ የሚወጣ እንጀራ ወፍራምና ብዙ ይሆናል። እህሉም ብዙ ይሆናል። በዚያም ቀን ከብቶችህ በሰፊ መስክ ይግጣሉ።
24መሬትንም የሚያርሱ በሬዎችና አህዮች በመንሽና በወንፊት የነጻውን ጨው ጨው የሚለውን ገፈራ ይበላሉ።
25በታላቅም እልቂት ቀን ግንቦች በወደቁ ጊዜ በረጅሙ ተራራ ሁሉ ከፍ ባለውም ኮረብታ ሁሉ ላይ ወንዞችና የውኃ ፈሳሾች ይሆናሉ።
26እግዚአብሔርም የሕዝቡን ስብራት በጠገነ ዕለት፣ መቅሰፍቱ ያቈሰለውንም በፈወሰ ዕለት፣ የጨረቃ ብርሃን እንደ ፀሐይ ብርሃን፣ የፀሐይም ብርሃን እንደ ሰባት ቀን ብርሃን ሰባት እጥፍ ይሆናል።
27ተመልከቱ፣ የእግዚአብሔር ስም ከሚነድድ ቍጣ ከሚትጐለጐልም ጢስ ጋር ከሩቅ ይመጣል፤ ከንፈሮቹም ቍጣን የተሞሉ ናቸው፣ ምላሱም እንደምትበላ እሳት ናት።
28እስትንፋሱም አሕዛብን በአጥፊ ወንፊት ሊነፋቸው እንደሚያጥለቀልቅ እስከ አንገትም እንደሚደርስ ወንዝ ነው፣ በሕዝብም መንጋጋ የሚያስት ልጓም ይሆናል።
29ዝማሬ በተቀደሰች የዐውደ ዓመት ሌሊት እንደሚሆን ዝማሬ ይሆንላችኋል፤ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ እስራኤል አምባ ይመጣ ዘንድ እንቢልታ ይዞ እንደሚሄድ ሰው የልብ ደስታ ይሆንላችኋል።
30እግዚአብሔርም ክቡር ድምፁን ያሰማል፣ የክንዱንም መውረድ በሚነድድ ቍጣውና በምትባላ እሳት ነበልባል፣ በዐውሎ ነፋስም በወጨፎም፣ በበረዶ ጠጠርም ይገልጣል።
31አሦርም በበትር ከመታው ከእግዚአብሔር ድምፅ የተነሣ ይደነግጣል።
32እግዚአብሔር በላዩ በሚያወርድበት የታዘዘበቱ የበትር ድብደባ ሁሉ በከበሮና በመሰንቆ ይሆናል፤ በጦርነትም ክንዱን አንሥቶ ይዋጋቸዋል።
33ከጥንት ጀምሮ የማቃጠያ ስፍራ ተዘጋጅታለች። በእርግጥ፣ ለንጉሥም ተበጅታለች፣ እግዚአብሔርም ጥልቅና ሰፊ አድርጎአታል። እሳትና ብዙ ማገዶ ተከምሮአል፤ የእግዚአብሔርም እስትንፋስ እንደ ዲን ፈሳሽ ያቃጥለዋል።