1ተመልከቱ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ድጋፍንና ብርታትን፡ የእንጀራን ድጋፍ ሁሉ የውኃውንም ድጋፍ ሁሉ ይወስዳል፤
2ኃያሉንም፣ ተዋጊውንም፣ ፈራጁንም፣ ነቢዩንም፣ ምዋርተኛውንም፣ ሽማግሌውንም፤
3የአምሳ አለቃውንም፣ ከበርቴ የሆነውን ዜጋ፣ አማካሪውንም፣ የብልኃት ሠራተኛውንም፣ አስማት አዋቂውንም ይነቅላል።
4"አለቆቻቸው እንዲሆኑ ተራ ወጣቶችን አስነሣባቸዋለሁ፣ ብላቴናውም ይገዛቸዋል።
5ሕዝቡም ይጨቆናሉ፣ ሰው በሰው ላይ፣ ሰውም በባልንጀራው ላይ ይገፋፋል፤ ብላቴናውም በሽማግሌው ላይ የተጠቃውም በከበርቴው ላይ ይኰራል።
6ሰውም በአባቱ ቤት ውስጥ ወንድሙን ይዞ፣ 'አንተ ልብስ አለህ፤ አለቃም ሁንልን፣ ይህችም ባድማ ከኃላፊነትህ በታች ትሁን' ይለዋል።
7በዚያ ቀን ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ ይላል፣ 'እኔ በቤቴ ውስጥ እንጀራ ወይም ልብስ የለኝምና ባለ መድኃኒት አልሆንም። በሕዝቡም ላይ አለቃ አታደርጉኝም" ይላል።
8ንጉሣዊ ሥልጣኑን ያረክሱ ዘንድ ንግግራቸውና ሥራቸው በእግዚአብሔር ላይ ነውና ኢየሩሳሌም ተፈታች ይሁዳም ወደቀ።
9የፊታቸውም እፍረት ይመሰክርባቸዋል፤ እንደ ሰዶምም ኃጢአታቸውን ያወራሉ፤ አይሠውሩአትም። በራሳቸው ላይ ጥፋትን ሠርተዋልና ለነፍሳቸው ወዮ!
10የሥራውን ፍሬ ይበላልና፣ ጻድቁን መልካም ይሆንልሃል በሉት።
11እንደ እጁ ሥራ ፍዳው ይደረግበታልና ለበደለኛ ወዮ! ክፉም ደርሶበታል።
12ሕዝቤን አስገባሪዎቻቸው ይገፉአቸዋል፣ ሴቶችም ይሠለጥኑባቸዋል። ሕዝቤ ሆይ፣ መሪዎቻችሁ ያስቱአችኋል የምትሄዱበትንም መንገድ አቅጣጫ ያጠፋሉ።
13እግዚአብሔር በፍርድ ቤት ሊፈርድ ተነሥቶአል፣ በሕዝቡም ላይ ሊፈርድ ቆሞአል።
14እግዚአብሔር ከሕዝቡ ሽማግሌዎችና ከአለቆቻቸው ጋር ይፋረዳል፡ "የወይኑን ቦታ የበላችሁ እናንተ ናችሁ፤ ከድሆች የበዘበዛችሁት በቤታችሁ አለ፤
15ሕዝቤንስ ለምን ታደቅቁአቸዋላችሁ? የድሆችንስ ፊት ለምን ትፈጫላችሁ?" ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
16ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፣ የጽዮን ቈነጃጅት ኰርተዋልና፣ አንገታቸውንም እያሰገጉ በዓይናቸውም እያጣቀሱ፣ ፈንጠርም እያሉ፣ በእግራቸውም እያቃጨሉ ይሄዳሉ።
17ስለዚህ ጌታ የጽዮንን ቈነጃጅት አናት በበሽታ ቡሀነት ይመታል፣ እግዚአብሔርም መላጣ ያደርጋቸዋል።
18በዚያም ቀን ጌታ የእግር አልቦውን ክብር፣ መርበብንም፣ ጨረቃ የሚመስለውንም ጌጥ፣
19የጆሮ እንጥልጥሉንም፣ አንባሩንም፣ መሸፈኛውንም፣
20ቀጸላውንም፣ የቁርጭምጭሚት ሰንሰለቱንም፣ መቀነቱንም፣ የሽቱውንም ዕቃ።
21አሸንክታቡንም፣ የእጅና የአፍንጫ ቀለበቱንም ያስወግዳል፤
22የዓመት በዓል ልብሶችን፣ መጐናጸፊያውንም፣ መሸፈኛውንም፣ ከረጢቱንም፤
23የእጅ መስተዋቱንም፣ ከጥሩ በፍታ የተሰራውንም ልብስ፣ ራስ ማሰሪያውንም፣ ዓይነ ርግቡንም ያስወግዳል።
24በሽቱ ፋንታ ግማት፣ በመታጠቂያውም ፋንታ ገመድ፣ ጠጕርንም በመንቀስ ፋንታ ቡሀነት፣ በመጐናጸፊያ ፋንታ ማቅ፣ በውበትም ፋንታ ጠባሳ ይሆናል።
25ጕልማሶችሽ በሰይፍ፣ ኃያላንሽም በውጊያ ይወድቃሉ።
26በሮችዋ ያዝናሉ ያለቅሱማል፤ እርስዋም ብቻዋን በምድር ላይ ትቀመጣለች።