መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 28

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ለኤፍሬም ሰካሮች ትዕቢት አክሊል፣ በወይን ጠጅ ለተሸነፉ በወፍራም ሸለቆአቸው ራስ ላይ ላለችም ለረገፈች ለክብሩ ጌጥ አበባ ወዮ!
2እነሆ፣ በጌታ ዘንድ ኃያል ብርቱ የሆነ አለ። እንደ በረዶ ወጨፎ፣ እንደሚያጠፋም ወጀብ፣ እንደሚያጥለቀልቅም እንደ ታላቅ ውኃ ፈሳሽ በጠነከረ እጅ ምድርን ያጠቃል።
3የኤፍሬም ሰካሮች ትዕቢት አክሊል በእግር ይረገጣል፤
4በወፍራሙ ሸለቆ ራስ ላይ ያለች የረገፈች የክብሩ ጌጥ አበባ፣ ከመከር በፊት አስቀድማ እንደምትበስል በለስ ትሆናለች፤ ሰው ባያት ጊዜ በእጁ እንዳለች ይበላታል።
5በዚያ ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለቀሩት ሕዝቡ የክብር ዘውድና የጌጥ አክሊል ይሆናል፤
6በፍርድ ወንበር ላይ ለሚቀመጥም የፍርድ መንፈስ፣ ሰልፉን ወደ በር ለሚመልሱም ኃይል ይሆናል።
7እነዚህም ደግሞ ከወይን ጠጅ የተነሣ ይስታሉ፤ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ። ካህኑና ነቢዩ ከሚያሰክር መጠጥ የተነሣ ይስታሉ፣ በወይን ጠጅም ይዋጣሉ። ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ፤ በራእይ ይስታሉ፣ በፍርድም ይሰናከላሉ።
8በእውነት፣ ገበታው ሁሉ ትውከትን ተሞልቷል፤ ንጹሕ ስፍራ እንኳ የለም።
9እውቀትን ለማን ያስተምረዋል፣ ወይስ መልእክቱን ለማን ያስረዳል? ወተትን ለተዉ ወይስ ጡትን ለጣሉ ነውን?
10ትእዛዝ በትእዛዝ ላይ፣ ትእዛዝ በትእዛዝ ላይ፣ ሥርዓት በሥርዓት ላይ፣ ደንብ በደንብ ላይ፣ እዚህ ጥቂት፣ ጥቂት በዚያ ነው።
11በእርግጥ፣ በፌዘኛ አፍ በሌሎችም ልሳን ለዚህ ሕዝብ ይናገራል፤
12"ይህች እረፍት ናት፣ የደከመውን አሳርፉ፤ ይህችም የምታድስ ማረፊያ ናት" አላቸው፤ እነርሱ ግን አልሰሙም።
13ስለዚህ ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ እንዲሰበሩም ተጠምደውም እንዲያዙ የእግዚአብሔር ቃል ትእዛዝ በትእዛዝ ላይ፣ ትእዛዝ በትእዛዝ ላይ፣ ሥርዓት በሥርዓት ላይ፣ ሥርዓት በሥርዓት ላይ፣ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ይሆንላቸዋል።
14ስለዚህ በኢየሩሳሌም ያለውን ይህንን ሕዝብ የምትገዙ ፌዘኞች ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
15እናንተም፣ "ከሞት ጋር ቃል ኪዳን አድርገናል፣ ከሲኦልም ጋር ተማምለናል፤ ስለዚህ ሐሰትን መሸሸጊያችን አድርገናልና፣ በሐሰትም ተሰውረናልና የሚትረፈረፍ መቅሠፍት ባለፈ ጊዜ አይደርስብንም" አላችሁ።
16ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። "ተመልከቱ፡ በጽዮን የመሠረት ድንጋይን አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን ድንጋይ፣ የከበረውን፣ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ። የሚያምን እርሱ አያፍርም።
17ለገመድ ፍርድን፣ ለቱንቢም ጽድቅን አደርጋለሁ። በረዶውም የሐሰትን መሸሸጊያ ይጠርጋል፣ ውኆችም መሰወሪያውን ያሰጥማሉ።
18ከሞትም ጋር ያደረጋችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል፣ ከሲኦልም ጋር የተማማላችሁት መሐላ አይጸናም። የሚትረፈረፍ መቅሠፍት ባለፈ ጊዜ ትረገጡበታላችሁ።
19ባለፈም ጊዜ ይወስዳችኋል፤ ማለዳ ማለዳ ቀንና ሌሊት ያልፋል፤ መልእክቱ በገባቸው ጊዜ ድንጋጤ ይሆናል።
20ሰው በእርሱ ላይ ተዘርግቶ ቢተኛ አልጋው አጭር ነው፤ ሰውም ሰውነቱን መሸፈን ቢወድድ ብርድልብሱ እጅግ ጠባብ ነው።"
21እግዚአብሔርም ሥራውን፣ ማለትም እንግዳ የሆነ ሥራውን ይሠራ ዘንድ፣ አድራጎቱንም ማለት ያልታወቀውን አድራጎቱን ያደርግ ዘንድ በፐራሲም ተራራ እንደ ነበረ ይነሣል፣ በገባዖንም ሸለቆ እንደ ነበረ ይቈጣል።
22አሁንም እስራት እንዳይጸንባችሁ አታፊዙ። በምድር ሁሉ ላይ የሚጸናውን የጥፋት ትእዛዝ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰምቻለሁና።
23በትኩረት አድምጡና ድምፄን ስሙ፤ ልብ አድርጉ ንግግሬንም ስሙ።
24በውኑ ገበሬ ሊዘራ ሁልጊዜ ያርሳልን? ወይስ ሁልጊዜ እርሻውን ይጎለጉላልን?
25እርሻውን ባስተካከለ ጊዜ ጥቁሩን አዝሙድ፣ ከሙኑንም፣ ስንዴውንም፣ በተርታ፣ ገብሱንም በስፍራው፣ አጃንም በደረጃው የሚዘራ አይደለምን?
26አምላኩ ያስታውቀዋል፣ በብልሃት ያስተምረውማል።
27በተጨማሪም፣ ጥቁሩ አዝሙድ በተሳለች መሄጃ አያስኬድም፣ የሰረገላም መንኰራኵር በከሙን ላይ አይዞርም፤ ነገር ግን ጥቁሩ አዝሙድ በሽመል ከሙኑም በበትር ይወቃል።
28የእንጀራ እህል ይደቅቃል፣ ነገር ግን ለዘላለም አያኬደውም፤ የሰረገላውን መንኰራኵርና ፈረሶቹን ምንም ቢያስኬድበት አያደቅቀውም።
29ይህም ደግሞ ድንቅ ምክር ከሚመክር በግብሩም ማለፊያ ከሆነው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ወጥቶአል።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።