1ስለ ራእይ ሸለቆ የተነገረ ዐዋጅ፤ እናንተ ሁላችሁ ወደ ቤት ሰገነት መውጣታቸሁ ምን ሆናችኋል?
2ጩኸትና ፍጅት የተሞላብሽ ከተማ፣ ደስታ ያለሽ ከተማ ሆይ፣ በአንቺ ውስጥ የተገደሉት በሰይፍ የተገደሉ አይደሉም፣ በሰልፍም የሞቱ አይደሉም።
3ገዚዎችሽ ሁሉ በአንድነት ሸሹ፣ ያለ ቀስትም ተማረኩ፤ ከሩቅ ሸሽተው ከአንቺ ዘንድ የተገኙት ሁሉ በአንድነት ታሰሩ።
4ስለዚህም፣ "ወደ እኔ አትመልከቱ፣ መራራ ልቅሶ አለቅሳለሁ፤ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ጥፋት ታጽናኑኝ ዘንድ አትድከሙ" አልሁ።
5ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የድንጋጤና የመረገጥ የድብልቅልቅም ቀን፣ የቅጥርም መፍረስ ወደ ተራራም መጮኽ በራእይ ሸለቆ ውስጥ ሆኖአል።
6ኤላምም ከሰዎች ሠረገለኞችና ከፈረሰኞች ጋር ሆኖ አፎቱን ተሸከመ፣ ቂርም ጋሻውን ገለጠ።
7መልካሞቹንም ሸለቆችሽን ሠረገሎች ሞሉባቸው፣ ፈረሰኞችም መቆሚያቸውን በበር ላይ አደረጉ።
8የይሁዳንም መጋረጃ ገለጠ፤ በዚያም ቀን በዱር ቤት የነበረውን የጦር ዕቃ ተመለከትህ።
9የዳዊትም ከተማ ፍራሾች እንደ በዙ አይታችኋል፣ የታችኛውንም ኵሬ ውኃ አከማችታችኋል።
10የኢየሩሳሌምን ቤቶች ቈጥራችሁ ቅጥሩንም ለማጥናት ቤቶችን አፈረሳችሁ።
11በአሮጌው ኵሬ ላለው ውኃ በሁለቱ ቅጥር መካከል መጠባበቂያ ማከማቻ ሠራችሁ፤ ይህን ያደረገውን ግን አልተመለከታችሁም፣ ቀድሞ የሠራውንም አላሰባችሁም።
12በዚያም ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወደ ልቅሶና ወደ ዋይታ ራስን ወደ መንጨትና ማቅንም ወደ መልበስ ጠራ።
13ነገር ግን ተመልከቱ፣ ሐሜትና ደስታ በሬውንና በጉንም ማረድ፣ ሥጋንም መብላት፣ የወይን ጠጅንም መጠጣት ሆነዋል። እናንተ፣ ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣ ብላችኋል።
14ይህም ነገር በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ጆሮ ተገለጠ፡- "እስክትሞቱ ድረስ ይህ በደል በእውነት አይሰረይላችሁም" ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
15የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ "በቤቱ ውስጥ ወደ ተሾመው ወደዚህ አዛዥ ወደ ሳምናስ ሂድ እንዲህም በለው፣
16"መቃብር በዚህ ያስወቀርህ ከፍ ባለው ስፍራ መቃብር ያሠራህ በድንጋይም ውስጥ ለራስህ መኖርያ ያሳነጽህ በዚህ ምን አለህ? በዚህስ በአንተ ዘንድ ማን አለ?"
17እነሆ፣ እግዚአብሔር ወርውሮ ይጥልሃል፣ ኃያል ሰውም አጠንክሮ ይወረውርሃል፤ በኃይል ይጎትትሃል።
18ጠቅልሎም ያንከባልልሃል ወደ ሰፊይቱም ምድር እንደ ኳስ ይጥልሃል። በዚያ ትሞታለህ በዚያም የክብርህ ሰረገላዎች ይሆናሉ። አንተ የጌታህ ቤት እፍረት ትሆናለህ!
19ከአዛዥነትህና ከጣቢያ ሥራህ አሳድድሃለሁ። ከሹመትህም ትወርዳለህ።
20በዚያም ቀን ባሪያዬን የኬልቅያስን ልጅ ኤልያቄምን እጠራለሁ፥
21መጐናጸፊያህንም አለብሰዋለሁ፣ በመታጠቂያህም አስታጥቀዋለሁ፣ ሹመትህንም በእጁ አሳልፌ እሰጠዋለሁ። በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ለይሁዳም ቤት አባት ይሆናል።
22የዳዊትንም ቤት መክፈቻ በጫንቃው ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ይከፍታል የሚዘጋም የለም እርሱም ይዘጋል የሚከፍትም የለም።
23በአስተማማኝ ስፍራ እንደ ችንካር እተክለዋለሁ፣ ለአባቱም ቤት የክብር ዙፋን ይሆናል።
24የአባቱንም ቤት ክብር ሁሉ ልጆቹንም የልጅ ልጆቹንም፣ ከጽዋ ዕቃ ጀምሮ እስከ ማድጋ ዕቃ ድረስ፣ ታናናሹን ዕቃ ሁሉ ይሰቅሉበታል።
25በዚያ ቀን፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ በታመነው ስፍራ የተከለው ችንካር ይወልቃል፤ ተሰብሮም ይወድቃል፣ በእርሱም ላይ የተሰቀለው ሸክም ይጠፋል እግዚአብሔር ተናግሮአልና።