መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 23

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ስለ ጢሮስ የተነገረ ሸክም። የተርሴስ መርከቦች ሆይ፣ አልቅሱ፤ ፈርሶአልና ቤት የለም፣ መግቢያም የለም፤ ከኪቲም አገር ጀምሮ ተገልጦላቸዋል።
2እናንተ በደሴት የምትኖሩ፣ በባሕርም የምትሻገሩ የሲዶና ነጋዴዎች፣ ወኪሎቻችሁ የሚያቀርቡላችሁ፣ ጸጥ በሉ።
3የሺሖር ዘርና የዓባይ ወንዝ መከር በብዙ ውኆች ላይ ገቢዋ ነበረ፤ እርስዋም የአሕዛብ መናገጃ ነበረች።
4እፈሪ፣ ሲዶና ሆይ፣ ባሕር ተናግሯልና፣ የባሕሩ ኃያል ተናግሯል። እንዲህ አለ፣ "አላማጥሁም፣ አልወለድሁምም፤ ጐበዛዝትንም አላሳደግሁም፤ ወጣት ሴቶችንም አላሳደግሁም" ብሎ ተናግሮአልና እፈሪ።
5ወሬዋ ወደ ግብጽ በደረሰ ጊዜ፣ በጢሮስ ወሬ ስለ እርሷ ምጥ ይይዛቸዋል።
6ወደ ተርሴስ ተሻገሩ፤ እናንተ በደሴት የምትኖሩ አልቅሱ።
7ደስተኛዋ ከተማ፣ ከቀድሞ ዘመን ጀምሮ የነበርሽ፣ ይህ ደርሶብሻልን፣ እንግዳ በሆነ ስፍራዎች ለመኖር እግሮችዋ ወደ ሩቅ ያፈለሱአት የደስታችሁ ከተማ ይህች ናትን?
8አክሊል ባስጫነች ከተማ ነጋዴዎችዋ ልዑላን በሆኑ፣ በእርስዋም የሚሸጡና የሚለውጡ የምድር ክቡራን የሆኑባት ጢሮስ ላይ ይህን የወጠነ ማን ነው?
9የክብርን ሁሉ ትዕቢት ይሽር ዘንድ የምድርንም ክቡራን ሁሉ ያስንቅ ዘንድ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወስኖታል።
10የተርሴስ ልጅ ሆይ፣ የሚከለክልሽ የለምና እንደ ዓባይ ወንዝ በአገርሽ ላይ እረሺ።
11እግዚአብሔር በባሕር ላይ እጁን ዘረጋ፣ መንግሥታትንም አናወጠ፤ ምሽጎችዋንም ያጠፉ ዘንድ እግዚአብሔር ስለ ከነዓን አገር አዘዘ።
12እርሱም፣ "አንቺ የተበደልሽ የሲዶና ድንግል ልጅ ሆይ፣ ተነሺ፣ ከእንግዲህ ወዲህ በድጋሚ ደስ አይልሽም፤ ወደ ኪቲም ተሻገሪ፣ በዚያም ደግሞ አታርፊም አለ።
13ተመልከቱ የከለዳውያን ሰዎች። ይህ ሕዝብ መኖሩ ይቆማል፤ አሦራውያን ለምድረ በዳ አራዊት ሰጥተውታል። የወረራ ግንቦቻቸውን ሠሩ፥ አዳራሾችዋንም አፈረሱ፣ የጥፋት ባድማም አደረጓት።
14እናንተ የተርሴስ መርከቦች ሆይ፣ ምሽጋችሁ ፈርሶአልና ዋይ በሉ።
15በዚያም ቀን፣ ጢሮስ እንደ ንጉሥ ቀናት ሁሉ ሰባ ዓመት ያህል የተረሳች ትሆናለች። ከሰባ ዓመት በኋላ ግን ለጢሮስ በጋለሞታ ዘፈን እንደሚሆን እንዲሁ ይሆናል።
16አንቺ የተረሳሽ ጋለሞታ ሆይ፣ መሰንቆ ያዢ፣ በከተማ ላይም ዙሪ፤ መታሰቢያም ይሆንልሽ ዘንድ ዜማን አሳምሪ ዘፈንሽንም አብዢ።
17ከሰባ ዓመትም በኋላ እግዚአብሔር ጢሮስን ይረዳታል፣ ወደ ተቀጠረችበት ትመለሳለች። ደግሞም በምድር ፊት ላይ ከሆኑ ከዓለም መንግሥታት ሁሉ ጋር ትገለሙታለች።
18ንግድዋና ዋጋዋ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል። ንግድዋም በልተው ይጠግቡ ዘንድ ማለፊያም ልብስ ይለብሱ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ለሚኖሩ ይሆናል እንጂ በዕቃ ቤትና በግምጃ ቤት ውስጥ አይከተትም።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።