1በባሕር አጠገብ ስላለው ስለ ምድረ በዳ የተነገረ ዐዋጅ። ዐውሎ ነፋስ ከኔጌቭ እንደሚወጣ፣ እንዲሁ ከሚያስፈራ አገር በምድረ በዳ አልፎ ይወጣል።
2የሚረብሽ ራእይ ተነገረኝ፤ ወንጀለኛው በወንጀል ይሠራል፣ አጥፊውም ያጠፋል። ኤላም ሆይ፣ ወደ ላይ ውጪ፣ ሜዶን ሆይ ክበቢ፤ ትካዜውን ሁሉ አስቀርቻለሁ።
3ስለዚህ ወገቤ በሕመም ተሞላ፤ እንደምትወልድ ሴት ምጥ ያዘኝ፤ ከሰማሁት የተነሣ ጎበጥኩ፤ ካየሁት ነገር የተነሣ ተረበሽኩ።
4ልቤ ተርበደበደ፣ መንቀጥቀጥ አስፈራኝ፤ የተመኘሁት ሌሊት የሚያንቀጠቅጠኝ ሆነብኝ።
5ማዕዱን ያዘጋጃሉ፣ ምንጣፉንም ይዘረጋሉ፣ ይበሉማል፣ ይጠጡማል፤ እናንተ ልዑላን ሆይ፣ ተነሡ፣ ጋሻውን በዘይት ቀቡ።
6ጌታ ያለኝ እንዲህ ነው፣ "ሂድ፣ ጉበኛም አቁም፣ የሚያየውንም ይናገር።
7በከብት የሚቀመጡትን፣ ሁለት ሁለት እየሆኑ የሚሄዱት ሠረገሎች፥ በአህዮች የሚጋልቡትንና በግመሎች የሚጋልቡትን ባየ ጊዜ፣ በጽኑ ትጋት አስተውሎ ተግቶም ያድምጥ።"
8ያየውም። ጌታ ሆይ፥ ቀኑን ሁሉ ዘወትር በማማ ላይ ቆሜአለሁ፥ ሌሊቱንም ሁሉ በመጠበቂያዬ ላይ ተተክያለሁ፣"
9እነሆም፣ በፈረሶች የሚቀመጡ፣ ሁለት ሁለት ሆነው የሚሄዱ ፈረሰኞች ይመጣሉ ብሎ ጮኸ፤ እርሱም መልሶ፣ "ባቢሎን ወደቀች፣ ወደቀች፣ የተቀረጹም የአማልክቶችዋ ምስሎች ሁሉ በምድር ላይ ተጥለው ደቀቁ" አለ።
10እናንተ በአውድማዬ ላይ የተወቃችሁ የአውድማዬ ልጆች ሆይ! ከእስራኤል አምላክ፣ ከሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሰማሁትን ነገርኋችሁ።
11ስለ ኤዶምያስ የተነገረ ዐዋጅ። አንዱ ከሴይር ይጣራል፣ "ጕበኛ ሆይ፣ ከሌሊቱ ምን ያክል ሰዓት ቀረ? ጕበኛ ሆይ፣ ከሌሊቱ ምን ያክል ሰዓት ቀረ?" ብሎ ጠራኝ።
12ጕበኛውም እንዲህ አለ፣ "ማለዳው ይመጣል፣ ድግሞም ምሽቱ፤ ብትጠይቁ፣ ጠይቁ፤ ተመልሳችሁም ኑ" አለ።
13ስለ ዓረብ የተነገረ ዐዋጅ። የዴዳናውያን ነጋዴዎች ሆይ፣ በዓረብ ዱር ውስጥ ታድራላችሁ።
14በቴማን የምትኖሩ ሆይ፣ ወደ ተጠሙት ሰዎች ውኃ አምጡ፣ እንጀራ ይዛችሁ የሸሹትን ሰዎች ተቀበሉአቸው።
15ከሰይፍ፣ ከተመዘዘው ሰይፍ፣ ከተለጠጠውም ቀስት ከጽኑም ሰልፍ ሸሽተዋልና።
16ጌታ ያለኝ እንዲህ ነውና፣ "ምንደኛ ለአንድ ዓመት እንደሚቀጠር፣ በአንድ ዓመት ውስጥ የቄዳር ክብር ሁሉ ይጠፋል፤
17ከቀስተኞች ቍጥር ጥቂቶቹ ብቻ፣ የቄዳር ልጆች ኃያላን፣ ያንሳሉ፤" የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።