መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 19

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ስለ ግብጽ የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል የሚከተለው ነው። ተመልከቱ፣ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ሆኖ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጻውያን ጣዖቶች በእርሱ ፊት ይናወጣሉ፤ የግብጽ ሕዝብም በፍርሃት ይቀልጣሉ።
2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ "ግብጻዊያንን በግብጻዊያን ላይ አስነሣለሁ፤ ወንድም በወንድሙ ላይ፣ ጐረቤትም በጐረቤቱ ላይ በጠላትነት እንዲነሣ አደርጋለሁ፤ ከተሞች በከተሞች ላይ፣ ነገሥታት በነገሥታት ላይ በጠላትነት ተነሥተው ይዋጋሉ።
3የግብጻውያን መንፈስ በውስጡ ይዳከማል። የጣዖቶቻቸውን የጠንቋዮቻቸውን የሙታን መናፍስት ጠሪዎችን ምክር ቢፈልጉም ምክሩን እደመስሳለሁ።
4እነርሱን በጭካኔ ለሚገዛቸው ጌታ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እኔ ጌታ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።"
5በዓባይ ውስጥ ያለው ውሃ ይደርቃል፣ ወንዙም እየደረቀ ሄዶ ባዶ ይሆናል
6ወንዞቹ ይገማሉ፤ የግብጽ ምንጭ እየጐደለ ይደርቃል፤ ደንገሎቹና ቄጤማዎቹ ይጠወልጋሉ።
7በዓባይ ወንዝ ዳርቻ ያለው ቄጤማ ሁሉ ይደርቃል፤ በወንዙ አጠገብ የተዘራውም ሰብል ሁሉ ደርቆ ወደ አፈርነት በመለወጥ ነፋስ ይወስደዋል።
8ዓሣ አጥማጆችና መንጠቆአቸውን ወደ አባይ ወንዝ የሚጥሉ ሁሉ ያዝናሉ፤ ያለቅሳሉም፤ መረቦቻቸውንም በውሃ ላይ የሚዘረጉ ተስፋ ይቈርጣሉ፤
9የተበጠረውን የተልባ እግር የሚሠሩ እና ቀጭን ሐር የሚሠሩ ያፍራሉ።
10የግብጽ ሸማኔዎች ግራ ይጋባሉ፤ ደመወዝተኞችም በውስጣቸው ያዝናሉ።
11በጾዓን ያሉ ልዑላን ፍጹም ሞኞች ናቸው። ጠቢባን የሆኑት የፈርዖን አማካሪዎች ምክር ትርጉም የለሽ ይሆናል። ለፈርዖን "እኔ የብልኅ ሰው ልጅ ነኝ የጥንት ነገሥታት ልጅ ነኝ እንዴት ይላሉ?"
12እንግዲያው እነዚያ ጠቢባን ወዴት ናቸው? የሠራዊት አምላክ በግብጽ ላይ ያቀደውን ይንገሩህ፣ ደግሞም ያሳውቁህ።
13የጾዓን ልዑላን ሞኞች ሆኑ፤ የሜምፊስ ልዑሎችም ተታለሉ፤ የነገዶችዋ ማእዘናት የሆኑት ግብጽን አሳትዋት።
14የተቀያየጠ ምክር እንዲሰጡ ያደረጋቸውም እግዚአብሔር ነው፤ በመጨረሻም ግብጽ በሁሉ ነገር በመሳሳት የገዛ ትውከቱ አዳልጦት እንደሚጥለው ሰካራም ትንገዳገዳለች።
15በግብጽ ራስም ሆነ ጭራ፣ የዘንባባ ዝንጣፊ ቢሆን ወይም ቄጤማ የሆነ ምንም ነገር ማድረግ አይችልም።
16በዚያ ቀን፣ ግብጻዊያን እንደ ሴቶች ይሆናሉ። በእነርሱ ላይ ከሚነሣው የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር የቅጣት እጅ አንጻር ይሸበራሉ፣ ደግሞም ይፈራሉ።
17ይሁዳ ለግብጽ ሕዝብ የምታንገዳግድ ትሆናለች። ማንኛውም ሰው ስለ እርሷ ሲያስታውሳቸው፣ ከእግዚአብሔር የመቅጣት እቅድ የተነሣ ይሸበራሉ።
18በዚያን ቀን በግብጽ ምድር ውስጥ የሚገኙ አምስት የዕብራውያን ቋንቋ የሚናገሩ ከተሞች ይኖራሉ፤ በዚያም የሚኖሩ ሕዝቦች በሠራዊት አምላክ ስም ይምላሉ፤ ከእነዚህ ከተሞች አንዲቱ የፀሐይ ከተማ ተብላ ትጠራለች።
19በዚያን ቀን በግብጽ ምድር መካከል ላይ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራል፤ እንዲሁም በግብጽ ጠረፍ ላይ ለእግዚአብሔር የተለየ የድንጋይ ዐምድ ይተከላል።
20እነርሱም የሠራዊት አምላክ በግብጽ ምድር ለመኖሩ ምልክትና ምስክር ይሆናሉ። ከጭቆና የተነሣ እግዚአብሔር እንዲረዳቸው በሚጠይቁበት ጊዜ፣ የሚታደጋቸውን አዳኝ ይልክላቸዋል፣ እርሱም ከጠላቶቻቸው ያድናቸዋል።
21እግዚአብሔር ለግብጽ ሕዝብ የታወቀ ይሆናል፤ ደግሞም በዚያን ጊዜ እነርሱ ያውቁታል። መሥዋዕትና መባም ያቀርቡለታል፣ ለእግዚአብሔርም ስእለት ይሳላሉ፤ ስእለታቸውንም ሁሉ ይፈጽማሉ።
22እግዚአብሔር ግብጻውያንን ይቀጣል፤ ነገር ግን መልሶ ይፈውሳቸዋል፤ ወደ እርሱ ይመለሳሉ፤ እርሱም ጸሎታቸውን ሰምቶ ይፈውሳቸዋል።
23በዚያን ጊዜ በግብጽና በአሦር መካከል አውራ ጎዳና ይከፈታል፤ አሦራዊያን ወደ ግብጽ፣ ግብጻዊያንም ወደ አሦር ይመጣሉ፤ ደግሞም ግብጻዊያን ከአሦራዊያን ጋር ያመልካሉ።
24በዚያን ቀን፣ እስራኤል ከግብጽና ከአሦር ጋር ሦስተኛ አገር ትሆናለች፤ እነዚህም ሕዝቦች በዓለም መካከል በረከት ይሆናሉ።
25የሠራዊት አምላክም፣ "እናንተ በግብጽ የምትኖሩ ሕዝቤ፣ የፈጠርኳችሁ አሦራውያንና የመረጥኳችሁ የእስራኤል ሕዝብ የተባረካችሁ ሁኑ" ይላቸዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።