1ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የክንፎች ድምፅ ለሚሰማባት አገር ወዮላት፤
2መልእክተኞችን ከደንገል በተሠራ ጀልባ በአባይ ወንዝ ላይ ለምትልከው አገር፤ ሕዝብዋ ረጃጅሞችና ቆዳቸው ለስላሳ፣ አገራቸው በወንዞች የተከፋፈለች፣ ጠንካሮችና ኃያላን በመሆናቸው በዓለም ሁሉ ወደሚፈሩት ሕዝቦች እናንት ፈጣን መልእክተኞች ሂዱ!
3በዓለም የምትኖሩ ሁሉ እና በምድር የምትኖሩ፣ በተራሮች ጫፍ ላይ የተተከለ የሰንደቅ ዓላማ ምልክት ሲውለበለብ አስተውሉ፤ መለከት ሲነፋ ስሙ።
4እግዚአብሔር ያለኝ ነገር እንዲህ ነው፣ "በቀትር ጊዜ በጸጥታ እንደምታበራ ፀሐይ፣ በመከርም ወራት በሞቃት ሌሊት እንደሚታይ ጤዛ ከሰማያዊ መኖሪያዬ ጸጥ ባለ መንፈስ ቊልቊል እመለከታለሁ።"
5የወይን መከር ከመሰብሰቡ በፊት አበቦች ረግፈው የወይን ፍሬ በሚበስልበት ጊዜ የወይን ሐረግ ቅርንጫፎች በስለት ተቈርጠው እንደሚጣሉ እርሱ የዚያችን አገር ሕዝብ ያጠፋል።
6በአንድነት ለተራራ ወፎችና ለምድረ በዳ አራዊት ይተዋሉ። በበጋ ወፎች፣ በክረምትም አራዊት ይቀራመቷቸዋል።
7የሠራዊት አምላክ በዓለም ሁሉ የመፈራት ግርማ ካላቸው፣ ቆዳቸው ለስላሳ፣ ቁመታቸው ረጅም ኀያላንና ብርቱዎች ከሆኑት፣ በወንዞች የተከፋፈለች ምድር ካላቸው ከእነዚያ ሕዝብ መባ የሚቀበልበት ጊዜ ይመጣል፤ እነርሱም የሠራዊት አምላክ ወደሚመለክባት ወደ ጽዮን ኰረብታ ይመጣሉ።