1ስለ ደማስቆ የተነገረ ሸክም። እነሆ፣ ደማስቆ ከእንግዲህ ከተማ አትሆንም፤ የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች።
2የአሮኤር ከተሞች ይጣላሉ። ለመንጋ ማሰማሪያ ሆናሉ፣ የሚያስፈራቸውም የለም።
3የተመሸጉ ከተሞች ከኤፍሬም ይጠፋሉ፣ መንግሥትም ከደማስቆ፤ የሶርያም ቅሬታ እንደ እስራኤል ልጆች ክብር ይሆናል ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
4በዚያም ቀን የያዕቆብ ክብር ይከሳል፣ የሥጋውም ውፍረት ይሸበሸባል።
5አጫጅ የቆመውን እህል በእጁ ሰብስቦ ዛላውን እንደሚያጭድ ይሆናል። በራፋይም ሸለቆ ቃርሚያ እንደሚለቅም እንዲሁ ይሆናል።
6ወይራ በተመታ ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ፍሬ በራሱ ላይ እንደሚቀር፥ አራት ወይም አምስት በዛፊቱ ጫፍ እንደሚገኝ፣ በእርሱ ዘንድ ቃርሚያ ይቀራል ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር።
7በዚያ ቀን ሰው ወደ ፈጣሪው ይመለከታል፣ ዐይኖቹም ወደ እስራኤል ቅዱስ ያያሉ።
8እጁም የሠራችውን መሠዊያ አይመለከትም፣ ጣቶቹም ወደ አበጁአቸው፣ ወደ አሼራ ዐምዶች ወይም ወደ ፀሐይ ምስሎች አያይም።
9በዚያም ቀን በእስራኤል ልጆች ፊት የአሞራውያንና የኤውያውያን ከተሞች እንደ ተፈቱ እንዲሁ ከተሞችህ ይፈታሉ ባድማም ይሆናሉ።
10የደኅንነትህን አምላክ ረስተሃልና፣ የብርቱነትህንም ዐለት አላሰብክምና። ስለዚህ ያማረውን ተክል ተክለሃል፣ እንግዳንም ዘር ዘርተሃል
11በዚያ ቀን ተክለህ ታጥርለትና ታበቅለዋለህ። ብዙም ሳይቆይ ዘርህ ያብባል፣ ነገር ግን መከሩ የሚሆነው በኀዘንና በጥልቅ ኃዘን ነው።
12ወዮላችሁ! እንደ ባሕር ሞገድ ድምፅ ለሚጮኹ፣ እንደ ኃይለኛም ውኃ ጩኸት ለሚጮኹ አሕዛብ!
13አሕዛብ እንደ ብዙ ውኃ ጩኸት ይጮኻሉ፣ እግዚአብሔር ግን ይገሥጻቸዋል። እነርሱም ወደ ሩቅ ይሸሻሉ፣ በተራራም ላይ እንዳለ እብቅ፣ በነፋስ ፊት ዐውሎ ነፋስ እንደሚያዞረው ትቢያ ይበተናሉ።
14በመሸ ጊዜ፣ ተመልከቱ፣ ድንጋጤ አለ፤ ከማለዳም በፊት አይገኙም። የዘረፉን ሰዎች እድል ፈንታ፣ የበዘበዙን ዕጣ ይህ ነው።