1በምድርም ላይ ለሠለጠነው አለቃ የበግ ጠቦቶችን በምድረ በዳ ካለችው ከሴላ ወደ ጽዮን ሴት ልጅ ተራራ ስደዱ።
2እንደሚበርር ወፍ፣ እንደ ተበተኑም ጫጩቶች፣ እንዲሁ የሞዓብ ሴቶች ልጆች በአርኖን መሻገሪያዎች ይሆናሉ።
3"መመሪያን ስጪ፣ ፍርድን አድርጊ፣ በቀትር ጊዜ ጥላሽን እንደ ሌሊት አድርጊ፤ የተሰደዱትን ሸሽጊ፣ የሸሹትን አትግለጪ።
4ከሞዓብ የተሰደዱት ከአንቺ ጋር ይኑሩ፤ ከሚያጠፋቸው ፊት መጋረጃ ሁኛቸው።" ጭቆናው ይቆማልና፣ ጥፋትም ይቆማልና፣ ይጨቍኑ የነበሩ ከምድር ይጠፋሉና።
5ዙፋንም በኪዳን ታማኝነት ይመሠረታል፤ ከዳዊት ድንኳን የሆነው በታማኝነት በዚያ ይቀመጣል። ፍርድን የሚሻ ጽድቅንም የሚያደርግ እንደመሆኑ ይፈርዳል።
6ስለ ሞዓብ ትዕቢት፣ ስለ እብሪተኝነቱ፣ ስለ ኵራቱና፣ ስለ ቁጣው ሰምተናል። ትምሕክቱ ባዶ ቃላት ናቸው።
7ስለዚህ ሞዓብ ስለ ሞዓብ ያለቅሳል፤ ሁሉም ያለቅሳል። ፈጽሞ ስለሚጠፋው ስለ ቂርሐራሴት የዘቢብ ጥፍጥፍ ታለቅሳላችሁ።
8የሐሴቦን እርሻዎችና የሴባማ ወይን ግንዶች ደርቀዋል። የአሕዛብ አለቆች የሰባበሩአቸው ቅርንጫፎች እስከ ኢያዜር ደርሰው ወደ ምድረ በዳ ተበትነዋል። ቍጥቋጦቹም ተንሰራፍተው ወደ ባሕር ሄደው ነበር።
9በእርግጥ በኢያዜር ልቅሶ ስለ ሴባማ ወይን ግንድ አለቅሳለሁ። ሐሴቦንና ኤልያሊ ሆይ፣ በእምባዬ አረሰርሳችኋለሁ። በበጋሽ ፍሬና በመከር ላይ የደስታን ጩኸት ትቻለሁና።
10ደስታና ሐሤትም ከፍሬያማው የእርሻ ደን ተወስዶአል፤ በወይኑም ቦታዎች ዝማሬና የደስታ እልልታ የለም። በመጥመቂያም ወይን የሚረግጥ የለም፤ የረጋጮቹን እልልታ አጥፍቻለሁ።
11ስለዚህ ልቤ ስለ ሞዓብ አንጀቴም ስለ ቂርሔሬስ እንደ መሰንቆ ትጮኻለች።
12ሞዓብም መጥቶ በኮረብታ መስገጃ ላይ ራሱን በደከመና ለጸሎት ወደ መቅደሱ በገባ ጊዜ፣ ጸሎቱ ምንም ነገር አያሳካም።
13እግዚአብሔር በሞዓብ ላይ አስቀድሞ የተናገረው ነገር ይህ ነው።
14አሁን ግን እግዚአብሔር፣ "በሦስት ዓመት ውስጥ እንደ ምንደኛ ዓመት የሞዓብ ክብርና የሕዝቡ ሁሉ ብዛት ይዋረዳል፣ ቅሬታውም እጅግ ያነሰና የተጠቃ ይሆናል" ይላል።