መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢሳይያስ 11

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፣ የሥሩም ቍጥቋጥ ፍሬን ያፈራል።
2የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ፣ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።
3እግዚአብሔርን በመፍራት ደስታውን ያያል፤ ዐይኑም እንደምታይ አይፈርድም፣ ጆሮውም እንደምትሰማ አይበይንም፤
4ነገር ግን ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል፣ ለምድርም የዋሆች በቅንነት ይበይናል። በአፉም በትር ምድርን ይመታል፣ በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል።
5የወገቡ መታጠቂያ ጽድቅ፣ የጎኑም መቀነት ታማኝነት ይሆናል።
6ተኵላ ከበግ ጠቦት ጋር ይኖራል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል፣ ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ ትንሽም ልጅ ይመራቸዋል።
7ላምና ድብ አብረው ግጦሽ ይውላሉ፣ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ያርፋሉ። አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል።
8ሕፃን በእባብ ጕድጓድ ላይ ይጫወታል፣ ጡት የጣለውም ሕፃን በእፉኝት ቤት ላይ እጁን ይጭናል።
9በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጐዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።
10በዚያም ቀን፣ ለአሕዛብ ምልክት ሆኖ ይቆማል። የእሴይን ሥር አሕዛብ ይፈልጉታል፣ ማረፊያውም የተከበረ ይሆናል።
11በዚያም ቀን፣ የቀረውን የሕዝቡን ቅሬታ ከአሦርና ከግብጽ፣ ከጳትሮስና ከኢትዮጵያ፣ ከኤላምና ከሰናዖር ከሐማትም፣ ከባሕርም ደሴቶች ይመልስ ዘንድ ጌታ እንደ ገና እጁን ይገልጣል።
12ለአሕዛብም ምልክትን ያቆማል፣ ከእስራኤልም የተጣሉትን ይሰበስባል፣ ከይሁዳም የተበተኑትን ከአራቱ የምድር ማዕዘኖች ያከማቻል።
13የኤፍሬምንም ምቀኝነት ያቆማል፣ ይሁዳንም የሚጠሉ ይቆረጣሉ። ኤፍሬምም በይሁዳ አይቀናም፣ ይሁዳም ኤፍሬምን አይጠላም።
14በምዕራብም በኩል በፍልስጥኤማውያን ጫንቃ ላይ እየበረሩ ይወርዳሉ፣ የምሥራቅንም ልጆች በአንድነት ይበዘብዛሉ። በኤዶምያስና በሞዓብም ላይ እጃቸውን ይዘረጋሉ፣ የአሞንም ልጆች ለእነርሱ ይታዘዛሉ።
15እግዚአብሔርም የግብጽን ባሕር ያጠፋል፤ በትኩሱም ነፋስ እጁን በኤፍራጥስ ወንዝ ላይ ያነሣል፣ ሰባት ፈሳሾች አድርጎም ይከፋፍለዋል፣ ስለዚህም በጫማ ሊሻገሩት የሚችሉት ይሆናል።
16ከግብጽም በወጣ ጊዜ ለእስራኤል እንደ ነበረው ሁሉ ለቀረውም ሕዝብ ቅሬታ ከአሦር የሚወጣበት ጐዳና እንዲሁ ይሆናል።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።