1እስራኤል ፍሬውን የሚሰጥ ያማረ ወይን ነው። ፍሬው በበዛ መጠን፥ መሠዊያ አብዝቶ ሠራ። ምድሩ አብዝቶ ባፈራ መጠን፥የተቀደሱ አ ምዶቹን አሳመረ።
2ልባቸው አታላይ ነው፥ አሁን በደላቸውን ሊሸከሙ ይገባል። እግዚአብሔር መሠዊያዎቻቸውን ያፈርሳል፤ የተቀደሱ አምዶቻቸውን ያጠፋል።
3አሁንም እነርሱ፦ «እግዚአብሔርን ስላልፈራን፥ ንጉሥ የለንም፤ ንጉሥሥ ምን ሊያደርግልን ይችል ነበር?» ይላሉ።
4ባዶ ቃላትን ይናገራሉ፥ በሐሠት መሃላም ኪዳን ያደርጋሉ። ስለዚህ ፍትሕ፥ በእርሻ ትልም ላይ እንደሚወጣ መርዛማ አረም ይወጣል።
5የሰማሪያ ነዋሪዎች ከቤትአዌን ጥጃዎች የተነሳ ይፈራሉ። በእነርሱና በውብታቸው ደስ ይሰኙ የነበሩ እነዚያ ጣዖት አምላኪ ካህናት እንደሚያልቅሱላቸው፣ ሕዝቡም ያለቅሱላቸዋል፤ ከእንግዲህ ወዲያ በዚያ የሉምና።
6ለታላቁ ንጉሥ እጅ መንሻ ወደ አሦር ይወሰዳሉ። ኤፍሬም ይዋረዳል፥ እስራኤልም የጣዖታትን ምክር በመከተሉ ያፍራል።
7የሰማርያ ንጉሥ፥ በውኃ ላይ እንዳለ የእንጨት ፍቅፋቂ ይጠፋል።
8የእስራኤል ኃጢአት የሆኑት፥ የክፋት ቅዱስ ቦታዎች ይጠፋሉ። እሾህና አሜክላ በመሠዊያዎቻቸው ላይ ይበቅላሉ። ሕዝቡ ተራሮችን፥ «ሸፍኑን!»፥ ኮረብታዎችንም፥ «ውደቁብን!» ይላሉ።
9እስራኤል ሆይ ከጊብዓ ዘመን አንስቶ ኃጢአት ሠራችሁ፥ በዚያም ጸንታችኋል። በጊብዓ ክፉ አድራጊዎች ላይ ጦርነት በድንገት አልደረሰባቸውምን?
10በወደድሁ ጊዜ እገሥጻቸዋለሁ። ሕዝቦች በአንድነት ይሰበሰቡባቸዋል፥ ስለ ድርብ ኃጢአታቸውም ያስሯቸዋል።
11ኤፍሬም እህል ማበራየት የምትወድ የተገራ ጊደር ነች፥ ስለዚህ በሚያምር ጫንቃዋ ላይ ቀንበር አኖራለሁ። በኤፍሬም ላይ ቀንበር አኖራለሁ፥ ይሁዳ ያርሳል፥ ያዕቆብም ብቻውን መከስከሻውን ይጎትታል።
12ጽድቅን ለራሳችሁ ዝሩ፥ የኪዳኑን ታማኝንት ፍሬም እጨዱ። እስኪመጣ፥ ጽድቅንም እስኪያዝንብባችሁ ድረስ እግዚአብሔርን የምትፈልጉበት ጊዜ ነውና፤ ያልታረሰ መሬታችሁን አለስልሱ።
13ክፋትን አረሳችሁ፥ግፍንም አጨዳችሁ። በስልታችሁና በወታደሮቻችሁ ብዛት ታምናችኋልና፥ የመታለልን ፍሬ በላችሁ።
14ስለዚህ በሕዝብህ መካከል የጦርነት ሽብር ይነሣል፥ የተመሸጉ ከተሞችህም ሁሉ ይጠፋሉ። እናቶች ከልጆቻችው ጋር እንደተከሰከሱበት፥ ስልማን በሰልፍ ቀን ቤትአርብኤልን እንዳጠፋበት ጊዜ ይሆናል።
15ስለዚህ ቤቴል ሆይ፥ ከታላቅ ክፋትሽ የተነሣ በአንቺም ላይ እንዲሁ ይሆናል። ንጋት ላይ የእስራኤል ንጉሥ ፈጽሞ ይጠፋል።»