1የመጀመሪያው ኪዳን ቢሆን በዚህ ምድር ለሚከናወነው አምልኮም ሆነ ለአምልኮ ደንቦች ስፍራ ነበረው።
2በመገናኛው ድንኳን የተዘጋጀ ቅድስት የተባለ ውጨኛ ክፍል ነበር። በዚህ ስፍራ መቅረዙ፣ ጠረጴዛውና የመንግስቱ መገለጫ ኅብስት ነበሩበት።
3ከሁለተኛው መጋረጃም በስተጀርባ ቅድስተ ቅዱሳን የተባለ ሌላ ክፍል ነበረ።
4ዕጣን ለማጠን የሚሆን የወርቅ መሠዊያ ነበረው። ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተለበጠ የኪዳን ታቦትም ነበረበት። በእርሱም ውስጥ መና ያለበት የወርቅ መሶብ፣ ያቆጠቆጠች የአሮን በትርና የኪዳኑ የድንጋይ ጽላቶች ነበሩት።
5በኪዳኑም ታቦት ላይ በስርየት መክደኛው ላ ያሰፈፉ የከበሩ የኩሩቤል ምስሎች ነበሩ። ይሁን እንጂ ስለ እነዚህ ሁሉ አሁን በዝርዝር መግለጽ አንችልም።
6እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከተዘጋጁ በኃላ፣ ካህናቱ አገልግሎቶቻቸውን ለመፈጸም በመደበኛነት በማደሪያው ድንኳን ውጫዊው ክፍል በኩል ይገባሉ።
7ሊቀ ካህናቱ ግን በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ሁለተኛው ክፍል ይገባል፣ በሚገባበትም ጊዜ ለራሱና ሕዝቡም ባለማወቅ ለፈጸሟቸው በደሎች የደም መሥዋዕት ይዞ እንጂ እንደዚሁ አይደለም።
8የመጀመሪያይቱ የመገናኛ ድንኳን በስፍራዋ ቆማ እስካለች ድረስ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚያመራው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ በምሳሌ እያሳየ ነው።
9ይህም ለአሁኑ ጊዜ ተምሳሌት ነው። አሁን እየቀረአቡ ያሉት ስጦታዎችም ይሁኑ መሥዋዕቶች የአምላኪውን ሕሊና ፍጹም ማድረግ የሚችሉ አይደሉም።
10ከተለያዩ የመንፃት ሥርዓቶች ጋር የተያያዙ ምግቦችና መጠጦች ብቻ ናቸው። እነዚህ ሁሉ አዲሱ ሥርዓት በሥራ ላይ እስኪውል ድረስ በሥጋዊ ደረጃ እንዲከበሩ የተሰጡ ሥርዓቶች ናቸው።
11ክርስቶስ በሰው እጆች በተሠራችው ሳይሆን ላቅ ባለችውና ይበልጥ ፍጹምና ቅድስት በመሆነችው፣ ከዚህም ከፍጥረታዊው ዓለም ባልሆነችው ድንኳን በኩል ለመጡት መልካም ነገሮች ሊቀ ካህናት ሆኖ መጥቷል።
12ክርስቶስ እጅግ ቅድስት ወደሆነችው ስፍራ አንድ ጊዜ ለሰዎች ሁሉ የገባውና የዘላለም ቤዛችንን ያስገኘልን በፍየሎችና በጥጃዎች ደም ሳይሆን በራሱ ደም ነው።
13የፍየሎችና የኮርማዎች ደም እንዲሁም የጊደሮች አመድ በሥርዓታዊ ደረጃ ንፁሕ ባልሆኑት ላይ መረጨቱ የሚያጠራቸውና ሰውነቶቻቸውንም ንፁሕ የሚያደርገው ከሆነ፣
14ይልቁንም ነውር ሳይኖረው በዘላለማዊ መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እናገለግል ዘንድ ሕሊናችንን ከሞተ ሥራ ምን ያህል ያነጻን ይሆን?
15ከዚህም የተነሳ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት በእግዚአብሔር የተጠሩት ስለ ዘላለም ርስት የተሰጣቸውን የስፋ ቃል ይቀበሉ አንድ በመጀመሪያው ኪዳን ሥር ከነበረባቸው የኃጢአት ቅጣት ነፃ እንዲወጡ የሞት ቅጣት ተፈጽሞ ስለነበረ ነው።
16ይህም የሆነው አንድ ሰው ኑዛዜ እንደተወ ሲገለጽ ኑዛዜ የተወውን ሰው መሞት ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።
17ምክንያቱም ኑዛዜ የሚጸናው ሞት ተከስቶ ከሆነ ብቻ ነው፣ ተናዛዡ በሕይወት እስካለ ሊጸና አይችልምና።
18እንደዚህም በመሆኑ የመጀመሪያው ኪዳን እንኳን ያለ ደም አልጸናምና።
19በሕጉ ውስጥ ያሉትን ማንኛቸውንም ትዕዛዛት ሙሴ ለሕዝቡ ሁሉ በሰጠ ጊዜ የጥጆችንና የፍየሎችን ደም ከውሃ፣ ከቀይ የበግ ፀጉርና ከሂሶጵ ጋር ቀላቅሎ በራሱ በሕጉ መጽሐፍና በሕዝብ ሁሉ ላይ ይረጭ ነበርና።
20ይህንንም ካደረገ በኃላ “እግዚቸብሔር ለእናንተ ሕግጋቱን የሰጠበት የኪዳኑ ደም ይህ ነው” ይል ነበር።
21በዚያው ዓይነት መንገድ ደሙን በመገናኛው ድንኳንና ለክህነት አገልግሎት በሚውሉት ዕቃዎች ሁሉ ላይ ይረጭ ነበር።
22ሕጉ በሚለውም መሠረት ሁሉም ነገር የሚነጻው በደም ነበር ማለት ይቻላል። ደምም ካልፈሰሰ በስተቀር ይቅርታ የለም።
23ስለሆነም በሰማይ ያሉት ነገሮች ግልባጮችም በእነዚህ የእንስሳት መሥዋዕቶች ይነጹ ዘንድ አስፈላጊ ነበር። ይሁን እንጂ ሰማያዊ የሆኑት ነገሮች ራሳቸው እጅግ በተሻሉ መሥዋዕት መንጻት ይገባቸዋል።
24ክርስቶስ በእጅ ወደተሠራው የእውነተኛውም ግልባጭ ብቻ ወደነበረው ቅድስተ ቅዱሳን አልገባምና። ይልቁንም እርሱ የገባው እግዚአብሔር ባለበት ስለ እኛ አሁን እግዚአብሔር ፊት ወደሚቀርብበት ሰማይ በቀጥታ ገብቷል።
25ወደዚያም የገባው የሌላውን ደም ይዞ በየዓመቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን እንደሚገባው እንደ ሊቀ ካህናቱ በየጊዜው ራሱን ለማቅረብ አይደለም።
26እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ከዓለም ጅማሬ አንስቶ ብዙ ጊዜ መከራ መቀበል ባስፈለገው ነበር። አሁን ግን ራሱን መሥዋዕት በማድረግ ኃጢአትን ለማስወገድ በዘመናት መጨረሻ የተገለጠው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
27እያንዳንዱ ሰው አንድ ጊዜ መሞት ከዚያ በኃላም ወደ ፍርድ መቅረብ እንደሚገባው ሁሉ
28እንደዚሁም የብዙዎችን ኃጢአት ለማስወገድ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበው ክርስቶስ ኃጢአትን ለማስወገድ ዓላማ ሳይሆን በትዕግሥት ለሚጠባበቁት ድነትን ያስገኝላቸው ዘንድ ዳግመኛ ይገለጣል