መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዕብራዊያን 10

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ሕጉ ሊመጡ ላሉ መልካም ነገሮች ጥላ ብቻ እንጂ እውነተኛው አካል አይደለም። ሕጉ ካህናት ያለማቋረጥ በየዓመቱ በሚያቀርቧቸው በነዚያው መሥዋዕቶች ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ከቶ ፍጹም ሊያደርጋቸው አይችልም።
2ቢችል ኖሮ እነዚያ መሥዋዕቶች መቅረባቸው ይቀር አልነበረምን? እንደዚያ ቢሆን ኖሮ የሚያመልኩት አንድ ጊዜ ከኃጢአታቸው ከነጹ በኋላ ስለ ኃጢአታቸው የሚያስታውሱት ነገር ምንም አይኖርም ነበር።
3-4ነገር ግን በእነዚያ መሥዋዕቶች ውስጥ በየዓመቱ የተፈጸሙትን ኃጢአቶች የሚያስታውስ ነገር አለ። ለዚህ ምክንያቱ የኮርማዎችና የበጎች ደም ኃጢአትን ማስወገድ ባለመቻሉ ነው።
5ክርስቶስ ወደ ዓለም ሲመጣ፣ “አንተ መሥዋዕቶችን ወይም ስጦታዎችን አልፈለግህም። ይልቅ ለእኔ ሥጋን አዘጋጀህልኝ።
6አንተ በሚቃጠል መባ ወይም በኃጢአት መሥዋዕት ደስ አልተሰኘህም።
7ቀጥሎም፣ “እግዚአብሔር ሆይ በመጽሐፍ ስለ እኔ እንደተጻፈው እነሆ ፈቃድህን ለማድረግ እዚህ አለሁ” ብሏል።
8ከላይ እንደተጠቀሰው፡“አንተ መሥዋዕቶችን፣ ስጦታዎችን ወይም ለኃጢአት የሚቃጠሉ ሙሉ መሥዋዕቶችን ማለትም በሕጉ መሠረት የሚቀርቡ መሥዋዕቶችን አልፈለግህ፣ በእነርሱም ደስ ስላልተሰኘህም” ብሏል።
9ደግሞም፣ “እነሆ ፈቃድህን ለማድረግ እዚህ አለሁ” አለ። ሁለተኛውን ሥርዓት ለመትከል የመጀመሪያውን ሥርዓት ወደ ጎን ያደርገዋል።
10በሁለተኛው ሥርዓት ለአንድ ጊዜና ለዘላለም በቀረበው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ አማካኝነት በእግዚአብሔር ፈቃድ ተቀድሰናል።
11በእርግጥ እያንዳንዱ ካህን ኃጢአትን ፈጽሞ ሊያስወግድ የማይችሉትን መሥዋዕቶች ለማቅረብ በየዕለቱ ለማገልገል ይቆማል።
12ነገር ግን ክርስቶስ ለኃጢአት ሁሉ ለዘላለም የሚሆን አንድ መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ፣
13ጠላቶቹ እስኪዋረዱና የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ እየተጠባበቀ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል።
14ይህም በአንድ መሥዋዕት የተቀደሱትን ለዘላለም ፍጹማን ስላደረጋቸው ነው።
15ደግሞም መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ይመሰክርልናል። ምክንያቱም በመጀመሪያ፣
16“ ከእነዚያ ቀኖች በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ቃልኪዳን ይህ ነው፡ ሕጎቼን በልባቸው ውስጥ አደርጋለሁ፣ ደግሞም በአእምሮአቸው ውስጥ እጽፈዋለሁ” ስላለ ነው።
17ቀጥሎም፣ “ኃጢአታቸውንና ዓመጻቸውን ከእንግዲህ አላስበውም” አለ።
18ለእነዚህ ነገሮች ይቅርታ በተረገበት በዚያ ለኃጢአት ከእንግዲህ ወዲያ መሥዋዕት አይቀርብም።
19ስለዚህ ወንድሞች፣ በኢየሱስ ደም አማካኝነት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የመግባት ድፍረት አለን።
20ይህም በመጋረጃው ማለትም በሥጋው አማካኝነት ለእኛ የከፈተልን አዲስና ሕያው መንገድ ነው።
21በእግዚአብሔር ቤት ታላቅ ካህን ስላለን፣
22ልባችን በመረጨት ከክፉ ኅሊና ሁሉ ነጽቶ፣ ሥጋችንም በንጹሕ ውኃ ታጥቦ ባገኘነው የእምነት ሙሉ ዋስትና በእውነተኛ ልብ እንቅረብ።
23ተስፋን የሰጠ እግዚአብሔር ታማኝ ስለሆነ፣ አምነን የምንመሰክረውን ተስፋ ያለ ማወላወል አጥብቀን እንያዝ።
24ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እርስ በርስ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ።
25አንዳንዶቹ ልማድ እንዳደረጉት በአንድነት መሰብሰባችንን አንተው። በዚህ ፈንታ ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችሁ ይበልጥ ተበረታቱ።
26የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ሆን ብለን ኃጢአት ማድረጋችንን የምንቀጥል ከሆንን፣ ከእንግዲህ ለኃጢአት የሚሆን መሥዋዕት አይኖርም።
27ይልቅ የሚጠብቀን የሚያስፈራ ፍርድና የእግዚአብሔርን ጠላቶች ሊበላ ያለ ብርቱ እሳት ብቻ ነው።
28የሙሴን ሕግ የናቀ ማናቸውም ሰው በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ያለ ምንም ምሕረት ይሞታል።
29ታዲያ የእግዚአብሔርን ልጅ የናቀ፣ የተቀደሰበትን የቃልኪዳኑን ደም እንደ እርኩስ የቆጠረ፣ የጸጋን መንፈስ የሰደበ ሰው ምን ያህል የባሰ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል?
30“በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ዋጋን እመልሳለሁ” ያለውን እናውቃለንና። ደግሞም፣ “ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል።”
31በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነገር ነው!
32ነገር ግን ከበራላችሁ በኋላ በእንዴት ያለ ታላቅ ሥቃይ ውስጥ እንደታገሣችሁ እነዚያን የቀደሙ ወቅቶች አስታውሱ።
33በስድብና በስደት ለሕዝብ መሳለቂያ ተዳርጋችኋል፣ ደግሞም በዚህ ዓይነቱ ሥቃይ ውስጥ ካለፉ ሰዎችም ጋር አብራችሁ ነበራችሁ።
34ለእስረኞች ርኅራኄ አሳያችሁ፣ የተሻለና ዘላለማዊ ሀብት ለራሳችሁ እንዳላችሁ በመረዳትም የንብረታችሁን መነጠቅ በደስታ ተቀበላችሁ።
35ስለዚህ ታላቅ ዋጋ ያለውን ድፍረታችሁን አትጣሉ።
36ፈቃዱን ካደረጋችሁ በኋላ እግዚአብሔር ለእናንተ ተስፋ የገባውን ነገር ለመቀበል መታገሥ ያስፈልጋችኋል።
37“በጣም በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚመጣው በእርግጥ ይመጣል፣ አይዘገይምም።
38የእኔ የሆነው ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል። ወደኋላ ቢመለስ በእርሱ ደስ አይለኝም።”
39እኛ ግን ለጥፋት ወደኋላ እንደሚያፈግፍጉት አይደለንም። ይልቅ እኛ ነፍሳቸውን ለማዳን ከሚያምኑት ነን።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።