መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዕብራዊያን 6

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ስለዚህ ስለ ክርስቶስ መልእክት በመጀመሪያ የተረዳነውን ተወት በማድረግ ወደ ብስለት ልንሻገር ይገባናል እንጂ ከሞተ ሥራ ንስሐ መግባትንና በእግዚአብሔር ማመንን፣
2ወይም ጥምቀቶችን፣እጆች መጫንን፣ የሙታን ትንሳኤን እንዲሁም የዘላለም ፍርድን ወደ ሚመለከት መሠረትን የመጣል ትምህርት መመለስ አይገባንም።
3እግዚአብሔር ከፈቀደ እነዚህንም እናደርጋለን
4ይህንን የምናደርገው አንድ ጊዜ ብርሃን በርቶላቸው ሰማያዊውን ስጦታ የተቀበሉትን፣ከመንፈስ ቅዱስ ተሳታፊዎች የነበሩትን፣
5መልካሙን የእግዚአብሔር ቃልና በመጪው ዘመን ሊመጣ ያለውን ኃይል ከቀመሱ በኃላ
6የካዱትን በንስሐ እንዲታደሱ ማድረግ የማይቻል በመሆኑ ነው። እነዚህ ለሕዝብ መሳለቂያ ይሆን ዘንድ ራሱን የእግዚአብሔርን ልጅ ራሳቸው እንደገና ይሰቅሉታል።
7በእርሷ ላይ ብዙ ጊዜ የሚዘንበውን ዝናብ ተቀብላ ለደከሙባት የሚጠቅም ፍሬን የምታፈራ መሬት ከእግዚአብሔር በረከትን ትቀበላለች።
8እሾህና አሜኬላ የምታበቅል ከሆነች ግን ዋጋ ቢስና እርግማን የሚጠብቃት ትሆናለች፣ ፍጻሜዋም መቃጠል ይሆናል።
9እንደዚህ የምንናገር ብንሆንም፣ ወዳጆች ሆይ፣ እናንተንና ድነታችሁን በሚመለከት ግን የተሻለ ነገር ስለ መኖሩ እርግጠኞች ነን።
10ምክንያቱም ቅዱሳንን በማገልገላችሁና አሁንም እያገለገላችኋቸው በመሆኑ ለስሙ ያላችሁን ፍቅር በማሳየት የሠራችሁትን ሥራ ይረሳ ዘንድ እግዚአብሔር ዓመፀኛ አይደለም።
11በፍጹም የመተማመን ዋስትና እያንዳንዳችሁ ይህንኑ ትጋት እስከመጨረሻ እንድታሳዩ በእጅጉ እንናፍቃለን።
12ከእምነትና ከትዕግሥት የተነሣ የተስፋ ቃሉን የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ቸልተኞች እንድትሆኑ አንፈልግም።
13ምክንያቱም እግዚአብሔር ለአብርሃም የተስፋ ቃል በገባለት ጊዜ ከራሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ
14“በእርግጥ እባርክሃለሁ፣ ዝርያዎችህንም እጅጉን አበዛለሁ” በማለት በራሱ ምሎአልና።
15በዚህ መንገድ በትዕግሥት ከጠበቀ በኃላ ተስፋ የተገባለትን ተቀበለ።
16ሰዎች ከእነርሱ በሚበልጠው ይምላሉና፣ በመካከላቸው ለሚፈጠርውም ለማንኛውም ሙግት መሐላ የመጨረሻው ማጽኛ ነው።
17የዓለማውን የማይለወጥ ባሕርይ ለተስፋው ወራሾች ይበልጥ ግልጽ አድርጎ ለማሳየት እግዚአብሔር በወሰነ ጊዜ በመሃላ አጸናው።
18ይህንን ያደረገው እግዚአብሔር ሊዋሽ በማይችልባቸው ሁለት የማይለወጡ ነገሮች በፊታችን ያለውን መተማመኛ አጥብቀን ይዘን አምባ ፍለጋ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ ድፍረት ይሆንልን ዘንድ ነው።
19ከመጋረጃው በስተጀርባ ወዳለው ቅድስት የሚገባውና እኛ የያዝነው ይህ መተማመኛ፣ ሥጋት የሌለበትና አስተማማኝ የነፍሶቻችን መልሕቅ ነው።
20በመልከ ጼዴቅ ሥርዓት ለዘላለም ሊቀ ካህናት በመሆን ኢየሱስ ወደዚህ ስፍራ ለእኛ ቀዳሚ በመሆን ገብቷል።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።