መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዕብራዊያን 12

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እንደነዚህ ያሉ እጅግ ብዙ ምስክሮች ስላሉን፣ የሚከብደንን ነገር ሁሉና በቀላሉ የሚጠላልፈንን ኃጢአት አሽቀንጥረን እንጣል። ከፊታችን ያለውንም ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ።
2በእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ ኢየሱስ ላይ ዓይኖቻችን እንትከል። እርሱ ከፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉንና መስቀሉ የሚያስከትለውን ውርደት ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል።
3እንዳትደክሙ ወይም ልባችሁ እንዳይዝል፣ ከኃጢአተኞች የተሰነዘረበትን እንዲህ ያለውን የጥላቻ ንግግር የታገሠውን እርሱን አስቡ።
4ደም እስከማፍሰስ ድረስ ኃጢአትን አልተቃወማችሁም፣ አልታገላችሁትምም።
5ደግሞም እንደ ልጆች፡ “ልጄ ሆይ የጌታን ቅጣት አታቅልል፣ በሚቀጣህም ጊዜ ልብህ አይዛል።
6ጌታ የሚወደውን ይገሥጻል፣ የሚቀበለውን ማንኛውንም ልጅ ይቀጣል" በማለት የተናገራችሁን ማበረታቻ ምክር ረስታችኋል።
7አባት በልጆቹ እንደሚደረግ እግዚአብሔርም በእናንተ ላይ ስለሚያደርግ፣ መከራን እንደ ተግሣጽ በመቁጠር ታገሡ። ለመሆኑ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው?
8ነገር ግን እኛ ሁላችን ከምንካፈለው ተግሣጽ ውጭ ከሆናችሁ፣ ዲቃሎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም።
9ከዚህም በላይ የሚቀጡን ምድራዊ አባቶች ነበሩን፤ እኛም እናከብራቸው ነበር። ይልቁንስ መንፈስ ለሆነው አባት እየታዘዝን መኖር የቱን ያህል ይገባናል?
10በእርግጥ አባቶቻችን ለእነርሱ መልካም መስሎ እንደታያቸው ለጥቂት ጊዜ ይቀጡን ነበር፣ እግዚአብሔር ግን የእርሱን የቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን ለጥቅማችን ያቀጣናል።
11ቅጣት በወቅቱ የሚያም እንጂ አስደሳች አይደለም። ይሁን እንጂ፣ ለለመዱት በመጨረሻ ሰላማዊ የጽድቅ ፍሬን ያፈራል።
12ስለዚህ የዛሉ እጆቻችሁን ወደ ላይ አንሡ፣ የደከሙ ጉልበቶቻችሁንም እንደገና አበርቱ፤
13የሚያነክስ ማንም ቢኖር እንዲፈወስ እንጂ እንዳይናጋ እግሮቻችሁ የሚራመዱባቸውን መንገዶች ቀና አድርጉ።
14ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ፣ ቅድስናንም ተከታተሉ፣ ያለ ቅድስና ማንም ጌታን ሊያይ አይችልም።
15ማንም ከእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጎድል፣ መራራ ሥርም አድጎ እንዳያስጨንቅና ብዙዎችን እንዳይመርዝ ተጠንቀቁ።
16ለአንድ መብል ብሎ ብኩርናውን እንደሸጠ እንደ ኤሳው እግዚአብሔርን የማይፈራ፣ ወይም ሴሰኛ የሆነ ማንም እንዳይኖር ተጠንቀቁ።
17ከዚያ በኋላ በረከትን ለመውረስ እያለቀሰ በትጋት ቢፈልግም፣ ከአባቱ ዘንድ የይቅርታ እድል እንዳጣና እንደተጣለ ታውቃላችሁ።
18የሚቃጠል እሳት፣ ጨለማ፣ ጭጋግና ማዕበል ወዳለበት በእጅ ሊነካ ወደሚችል ተራራ ገና አልመጣችሁም።
19የሰሙትም ሌላ ቃል እንዳይነገራቸው እስከሚለምኑ ወዳደረሳቸው ቃልን ወደሚያሰማ ድምጽ ወይም የመለከት ጩኹት ገና አልመጣችሁም።
20ይህም፣ “እንስሳም እንኳ ቢሆን ተራራውን ከነካ በድንጋይ ይወገር” ተብሎ የተሰጠውን ትእዛዝ ሊሸከሙት አልቻሉም።
21ሙሴ፣ “እጅግ ስለፈራሁ እየተንቀጠቀጥሁ ነኝ” እስከሚል ድረስ ይህ ስፍራ አስፈሪ ነበር።
22አሁን ግን፣ የሕያው እግዚአብሔር ከተማ ወደሆነችው ወደ ጽዮን ተራራ፣ አእላፋት መላእክት በደስታ ወደሚያመልኩባት ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም መጥታችኋል፤
23በሰማይ ወደሚገኙት የበኩራን ሁሉ ጉባኤ፣ የሁሉም ፈራጅ ወደሆነው እግዚአብሔርና ፍጹም የተደረጉ የጻድቃን መንፈሶች ወዳሉበት መጥታችኋል፤
24የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ወደሆነው ኢየሱስና ከአቤል ደም የተሻለውን ወደሚናገር ወደተረጨው ደም ደርሳችኋል።
25የሚናገራችሁን እምቢ እንዳትሉ ተጠንቀቁ። እነርሱ በምድር ላይ ሆኖ ያስጠነቀቃቸውን እምቢ በማለታቸው ካላመለጡ፣ በሰማይ ሆኖ ከሚያስጠነቅቀን በእርግጥ አናመልጥም።
26በዚያን ጊዜ ድምጹ ምድርን አናወጠ። ነገር ግን፣ “አንድ ጊዜ ደግሜ ምድርን ብቻ ሳይሆን ሰማያትንም አናውጣለሁ” በማለት አሁን ተስፋ ሰጥቷል።
27“አንድ ጊዜ ደግሜ” የሚል ቃል፣ ያልተናወጡ ነገሮች መጽናታቸውን፣ የተናወጡት ማለትም የተፈጠሩት ነገሮች መወገዳቸውን ያመላክታል።
28ስለዚህ፣ ሊናወጥ የማይችል መንግሥት ስለተቀብልን አምላካችንን እናመስግነው፣ ደግሞም እግዚአብሔርን ተቀባይነት ባለው በአክብሮትና በፍርሃት እናምልከው፣
29ምክንያቱም አምላካችን የሚባላ እሳት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።