መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዕብራዊያን 11

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እንግዲህ እምነት ሰው በተስፋ ለሚጠበቀው ነገር ማረጋገጫ ያልታየውም ነገርም አስረጅ ነው።
2የቀድሞ አባቶቻችንም እምነታቸው የተረጋገጠው በዚሁ ነበር።
3ፍጥርተ-ዓለሙ በእግዚአብሔር ትእዛዝ መፈጠሩን፣ የሚታየውም ከሚታዩት ነገሮች የተፈጠረ አለመሆኑን በእምነት እንረዳለን።
4አቤል ከቃየል የበለጠ ተቀባይነት ያለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቀረበው በእምነት ነበር። ጻድቅ እንደሆነ የተመሰከረለትም በዚህ ምክንያት ነበር። ስላቀረባቸው መሥዋዕቶች እግዚአብሔር መስክሮለታል። ቢሞትም እንኳ አሁንም ይናገራል።
5ሄኖክ ሞትን ሳያይ ወደ ላይ የተወሰደው በእምነት ነበር። “እግዚአብሔር ስለወሰደው አልተገኘም።” ከመወሰዱ በፊት እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተነግሮለታና።
6ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም፣ ወደ እግዚአብሔር የሚመጣ፣ እግዚአብሔር እንዳለና እርሱን ለሚሹትም ዋጋን እንደሚሰጥ ማመን ስለሚገባው ነው።
7ኖኅ ገና ስላልታዩ ነገሮች ከእግዚአብሔር ሲያስጠነቅቀው እግዚአብሔርን በመፍራት ቤተሰቡን የሚያድንበትን መርከብ የሠራው በእምነት ነበር። ይህን በማድረግ ዓለምን ኮንኖ በእምነት የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ።
8አብርሃም በተጠራ ጊዜ ርስትን ወደሚቀበልበት ቦታ ታዞ የሄደው በእምነት ነበር። የወጣው ወዴት እንደሚሄድ ሳያውቅ ነበር።
9በተስፋው ምድር እንደ ባዕድ የኖረውም በእምነት ነበር። ያን ተስፋ ከእርሱ አብረው ከሚወርሱት እንደ ይስሐቅና እንደ ያዕቆብ በድንኳን ውስጥ ኖረ።
10ይሄውም እግዚአብሔር መሠረት ያላትን፣ ያቀዳትንና ያነጻትን ከተማ ይጠባበቅ ስለነበር ነው።
11አብርሃምና ሣራ እጅግ አርጅተው ሳሉ እንደሚወልዱ በተነገራቸው ጊዜ፣ ወንድ ልጅን እንደሚሰጣቸው ተስፋ የገባላቸውን እግዚአብሔር ታማኝ አድርገው ስለቆጠሩ ሣራ ለማርገዝ ኃይል ያገኘችው በእምነት ነበር።
12በመሆኑም፣ ሊሞት ከተቃረበ ከዚህ አንድ ሰው ቁጥር ስፍር የሌላቸው ዝርያዎች ተገኙ። እነርሱም በሰማይ እንዳሉ ከዋክብትና በባሕር ጠረፍ እንዳለ አሸዋ በዙ።
13እነዚህ ሁሉ የተሰጧቸውን ተስፋዎች ሳይጨብጡ እምነታቸውን እንደጠበቁ ሞቱ። ይልቁንም እነዚህን ተስፋዎች ከሩቅ አይተው ስለተቀበሏቸው በምድር ላይ እንግዶችና መጻተኞች መሆናቸውን ተገነዘቡ።
14እንደዚህ የሚሉ ሰዎች የራሳቸው የሆነ አገር እንዲሚሹ በግልጽ ያሳያሉ።
15በእርግጥ ለቀው የመጡትን አገር ቢያሰቡ ኖሮ ለመመለስ ዕድሉ ነበራቸው።
16አሁን ግን የሚፈልጉት የተሻለውን ሰማያዊ አገር ነው። ስለዚህም፣ እግዚአብሔር ከተማን ስላዘጋጀላቸው አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ አያፍርም።
17አብርሃም በተፈተነ ጊዜ ይስሐቅን ያቀረበው በእምነት ነበር። አዎን፣
18“ዝሮችህ የሚጠሩት በይስሐቅ ነው” የተባሉለትን ተስፋዎቹን በደስታ ስለተቀበለ አንድ ልጁን ለመሥዋዕት አቀረበ።
19አብርሃም፣ እግዚአብሔር ይስሐቅን ከሞት ሊያስነሣ እንደሚችል አምኖ ነበር። ይስሐቅን ከሞት የመነሣት አምሳያ አድርጎ መልሶ ተቀበለው።
20ይስሐቅ ገና ወደፊት የሚመጡትን ነገሮች አስቦ ያዕቆብንና ኤሳውን በእምነት ባረካቸው።
21ያዕቆብ ፍጻሜው በተቃረበ ጊዜ፣ የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን የባረካቸውና በምርኩዙ አናት ተደግፎ የሰገደው በእምነት ነበር።
22ዮሴፍ ሊሞት ሲቃረብ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ እንደሚወጡ የተናገረውና የእርሱን አጽሙን እንዲወስዱ ያዘዘው በእምነት ነበር።
23ሙሴ ሲወለድ ወላጆቹ መልከ መልካም ሕፃን መሆኑን አይተው የንጉሡን ትእዛዝ ሳይፈሩ ለሦስት ወራት የደበቁት በእምነት ነበር።
24ሙሴም ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ፣ እንዳይባል እምቢ ያለው በእምነት ነበር።
25ለአጭር ጊዜ በኃጢአት ደስ ከመሰኘት ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መካፈልን መረጠ።
26ዓይኖቹ ወደፊት የሚቀበለውን ዋጋ አተኩረው ስለተመለከቱ፣ በግብጽ ከሚገኝ ሀብት ይልቅ ክርስቶስን መከተል የሚያስከትልበትን ውርደት የላቀ ብልጽግና አድርጎ አሰበ።
27ሙሴ ግብጽን ለቆ የወጣው በእምነት ነበር። የማይታየውን እርሱን ተመልክቶ በአቋሙ ስለጸና የንጉሡን ቁጣ አልፈራም።
28ቀሳፊው የእስራኤልን የበኩር ልጆች እንዳይነካ ሙሴ የፋሲካ በዓልንና የደም ርጭት ሥርዓትን ያካሄደው በእምነት ነበር።
29እስራኤላውያን በደረቅ መሬት ላይ እንደሚሄዱ ቀይ ባሕርን የተሻገሩት በእምነት ነበር። ግብጻውያን ይህን ለማድረግ በሞከሩ ጊዜ ተዋጡ።
30የኢያሪኮ ግንብ በእምነት የወደቀው ለሰባት ቀናት ከተከበበ በኋላ ነበር።
31ሴተኛ አዳሪዋ ረዓብ ሰላዮቹን ለደህንነታቸው ተጠንቅቃ ስለተቀበለቻቸው ከማይታዘዙት ጋር ያልጠፋችው በእምነት ነበር።
32-33እንግዲህ ከዚህ የበለጠ ምን ልበል? በእምነት መንግሥታትን ድል ስላደረጉት፣ ፍትህን ስላስከበሩትና የተስፋ ቃሎችን ስለተቀበሉት ስለነጌደዎን፣ ባርቅ፣ ሳምሶን፣ ዮፍታሄ፣ ዳዊት፣ ሳሙኤልና ነቢያት እንዳልናገር ጊዜ ያጥረኛል።
34እነርሱ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፣ የእሳትን ኃይል አጠፉ፣ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፣ ከበሽታ ተፈወሱ፣ በጦርነት ኃያላን ሆኑ፥ የባዕድን ሠራዊት አባረሩ።
35ሴቶች ሙታናቸው ከሞት ተነሡላቸው። ሌሎች የተሻለውን ትንሣኤ ያገኙ ዘንድ ከእስር መፈታታቸውን ለመቀበል እምቢ በማለት ተሠቃዩ።
36የተቀሩት ደግሞ በስድብና በግርፋት፣ እንዲያውም በሰንሰለት በመታሰር ተሠቃዩ።
37በድንጋይ ተወገሩ። በመጋዝ ለሁለት ተሰነጠቁ። በሰይፍ ተገደሉ። ይህ ዓለም ስላልተገባቸው
38በምድረበዳ፣ በተራሮች፣ በዋሻዎችና በየጉድጓዱ እየተጎሳቆሉ፣ መከራ እየተቀበሉና ግፍ እየተፈጸመባቸው የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው በመንከራተት ዞሩ።
39እነዚህ ሰዎች ሁሉ ስለ እምነታቸው በእግዚአብሔር ዘንድ የተመሰከረላቸው ቢሆኑም የተሰጣቸውን ተስፋ አልተቀበሉም።
40እነርሱ ያለ እኛ ፍጹም ስለማይሆኑ እግዚአብሔር ለእኛ የተሻለውን ነገር አስቀድሞ ሰጠን።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።