መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዕብራዊያን 13

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በወንድማማችነት ፍቅር መዋደዳችሁን ቀጥሉ።
2እንግዶችን መቀበል አትርሱ፣ አንዳንድ ሰዎች ይህን ሲያደርጉ ሳያውቁት መላእክትን አስተናግደዋል።
3ከእነርሱ ጋር እንደታሰረ ሆናችሁ፣ በሰውነታችሁም እንደ እነርሱ መከራን እንደሚቀበል ሆናችሁ በእስራት ያሉትን አስቡ።
4ጋብቻ በሁሉም ዘንድ የተከበረ መኝታውም ንጹሕ ይሁን፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር በሴሰኞችና በአመንዝራዎች ላይ ይፈርድባቸዋል።
5አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር የጸዳ ይሁን። እግዚአብሔር ራሱ፣ “እኔ ፈጽሞ አልተውህም፣ ደግሞም አልጥልህም” ስላለ፣ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ።
6ስለዚህ፣ “ጌታ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰውስ ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” ብለን በድፍረት እንናገራለን።
7የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን መሪዎቻችሁን አስቡ፣ የምግባራቸውንም ፍሬ ተመልከቱ፤ በእምነታቸውም ምሰሏቸው።
8ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንት፣ ዛሬና ለዘላለምም ያው ነው።
9በልዩ ልዩ እንግዳ ትምህርቶች አትወሰዱ፣ ለሚከተሏቸው ሰዎች ፋይዳ የሌላቸውን የአመጋገብ ሥርዓቶች በመጠበቅ ሳይሆን ልብ በጸጋ ሲጸና መልካም ነው።
10በመገናኛው ድንኳን የሚያገለግሉት ከእርሱ እንዲበሉ ያልተፈቀደላቸው መሠዊያ አለን።
11ሊቀካህናቱ ለኃጢአት ስርየት የተሠዋውን የእንስሳት ደም ወደ ቅድስት ያመጣል፣ የእንስሳቱ ሥጋ ግን ከሰፈር ውጭ ይቃጠላል።
12ደግሞም ኢየሱስ ሰዎችን በገዛ ደሙ ለመቀደስ ከከተማይቱ ቅጥር ውጭ መከራን ተቀበለ።
13ስለዚህ እኛም እርሱ የተሸከመውን ውርደት ተሸክመን ከሰፈር ውጭ ወደርሱ እንሂድ።
14በዚህ ምድር ምንም ዓይነት ዘላቂ ከተማ የለንም። ነገር ግን የምትመጣውን ከተማ እንጠብቃለን።
15የስሙን ታላቅነት የሚናገሩ የከንፈሮቻችንን ፍሬ፣ ማለትም የምስጋና መሥዋዕቶችን ያለማቋረጥ በኢየሱስ በኩል ለእግዚአብሔር ማቅረብ ይገባናል።
16ደግሞም መልካም ማድረግንና እርስ በርስ መረዳዳትን አትርሱ፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚደሰተው እንደነዚህ ባሉ መሥዋዕቶች ነው።
17ተጠያቂነት ስላለባቸው ለነፍሳችሁ እንክብካቤ ለሚያደርጉ ለመሪዎቻችሁ ታዘዙ፣ ተገዙላቸውም። ለእናንተ ስለማይጠቅም በሐዘን ሳይሆን በደስታ እንዲንከባከቧችሁ ታዘዟቸው።
18በሁሉም ነገር የከበረ ሕይወት ለመኖር የሚፈልግ ንጹሕ ኅሊና ስላለን ጸልዩልን።
19ወደ እናንተ ቶሎ መመለስ እንድችል ይበልጥ ይህን እንድታደርጉ አበረታታችኋለሁ።
20-21እንግዲህ በዘላለም ኪዳን ደም የበጎች ታላቅ እረኛ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስን፣ ከሙታን ያስነሣው የሰላም አምላክ እግዚአብሔር፣በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በእኛ ውስጥ የሚሠራውን፣ በእርሱ ፊት ደስ የሚያሰኘውን ፈቃዱን እንድታደርጉ በማናቸውም መልካም ነገር ያስታጥቃችሁ። ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ክብር ይሁን። አሜን።
22ወንድሞች ሆይ፤ አሁን በዐጭሩ የጻፍሁላችሁን ማበረታቻ እንድትቀበሉ አደፋፍራችኋለሁ።
23ወንድማችን ጢሞቴዎስ እንደተፈታ ዕወቁ፣ ቶሎ ከመጣም ከእርሱ ጋር አብሬ አያችኋለሁ።
24ለመሪዎችና ለቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ። በኢጣልያ ያሉት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
25ጸጋ ከሁላችሁም ጋር ይሁን።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።