1በጥበቃ ቦታዬ እቆማለሁ፤ በመጠበቂያው ግንብ ላይ ቦታዬን እይዛለሁ፤ ምን እንደሚለኝና ለጥያቄዬ ምን መልስ እንደሚሰጥ እጠባበቃለሁ፡፡
2ያህዌ እንዲህ በማለት መለሰልኝ፤ «ይህን ራእይ ጻፈው፤ በቀላሉ እንዲነበብ አድርገህም በጽላት ቅረጸው፡፡
3ራእዩ የሚናገረው ገና ወደ ፊት ስለሚሆነው ነው፡፡ በመጨረሻም ይፈጸማል እንጂ፣ በፍጹም አይዋሽም፡፡
4ተመልከት! ጠማማ ሐሳብ ያለው ሰው ታብዮአል፡፡ ጻድቁ ግን በእምነቱ ይኖራል፡፡
5ዐርፎ እንዳይቀመጥ ወይን ጠጅ ዕብሪተኛውን ወጣት አስቶታል ይልቁን ምኞቱን እንደ መቃብር አስፍቶአል እንደ ሞት በቃኝ ማለትን አያውቅም፡፡ ሕዝቦችን ሁሌ ወደ ራሱ ይሰበስባል ሰዎችንም ሁሉ ማርኮ ይወስዳል፡፡
6ታዲያ፣ በእንዲህ ዐይነቱ ሰው ላይ በማፌዝና በመዘባበት እንዲህ እያሉ ሁሉም አይሣለቁበትምን? ‹የተሰረቀውን ለራሱ ለሚያከማች፣ ራሱን በዐመፅ ባለጠጋ ለሚያደርግ ወዮለት! ይህ የሚቀጥለውስ እስከ መቼ ነው?
7በአንተ የተመረሩ ድንገት አይነሡብህምን፣ አንተን የማያስደነግጡስ አይነቁብህምን? በእጃቸውም ትወድቃለህ፡፡
8አንተ ብዙ ሕዝብ ስለ ዘረፍህ የተረፉት ሕዝቦች ይዘርፉሃል፡፡ የሰው ደም አፍስሰሃል አገሮች፣ ከተሞችና የሚኖሩባቸው ሰዎች ሁሉ ላይ ግፍ ሠርተሃል፡፡
9በማጭበርበር በተገኘ ሀብት ቤቱን ለሚገነባ ከክፉ ለማምለጥ ቤቱን በከፍታ ላይ ለሚሠራ ወዮለት!
10ብዙ ሰዎችን ለማጥፋት ደባ ፈጽመሃል በገዛ ቤትህ ላይ ውርደትን፣ በራስህም ላይ ኃጢአትን አድርገሃል፡፡
11ድንጋዮች በቅጥሩ ውስጥ ይጮኻሉ፣ ከዕንጨት የተሠሩ ተሸካሚዎችም እንዲህ በማለት ይመልሱላቸዋል፣
12«ደም በማፍሰስ ከተማን ለሚሠራ፣ በወንጀልም አገርን ለሚመሠርት ወዮለት!»
13ሰዎች ለእሳት ማገዶ እንዲሆን እንዲለፉ፣ ሕዝቦችም በከንቱ እንደደከሙ፣ የሰራዊት ጌታ ያህዌ ወስኖ የለምን?
14ያም ሆኖ፣ ውሃ ባሕርን እንደሚሞላ ሁሉ ምድርም የያህዌን ክብር በማወቅ ትሞላለች፡፡
15ኅፍረተ ሥጋቸውን ለማየት ባልንጀሮቹን ለሚያጠጣ፣ እስኪሰክሩም ድረስ ወይን ለሚያቀርብላቸው ወዮለት!»
16በክብር ፈንታ ውርደት ትሞላለህ፤ አሁን ተራው የአንተ ነውና ጠጣ፤ ኀፍረተ ሥጋህም ይገለጥ፤ በያህዌ ቀኝ እጅ ያለው ጽዋ በተራው ይመልስብሃል ክብርህን ውርደት ይሸፍነዋል፡፡
17ሊባኖስ ላይ ያሠራኸው ግፍ ያጥለቀልቅሃል፤ እንስሶች ላይ የፈጸምኸው ጥፋት ያስደነግጥሃል፡፡ የሰው ደም አፍስሰሃል፤ አገሮች፣ ከተሞችና የሚኖሩባቸው ሰዎች ሁሉ ላይ ግፍ ሠርተሃል፡፡
18ታዲያ፣ የቀረጽኸው ምስል ምን ይጠቅምሃል? ምስሉን የቀረጸው፣ ከቀለጠ ብረት ጣዖት የሠራ ሰው የሐሰት መምህር ነው፤ እነዚያን የማይናገሩ አማልክት ሲሠራ በገዛ እጅ ሥራው ተማምኖአልና፡፡
19ዕንጨቱን ንቃ! ሕይወት የሌለውንም ድንጋይ ተነሣ ለሚል ወዮለት ለመሆኑ፣ እነዚህ ነገሮች ማስተማር ይችላሉን? በወርቅና በብር ተለብጦአል፤ እስትንፋስ ግን የለውም፡፡
20ያህዌ ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለ፤ ምድር ሁሉ በፊቱ ጸጥ ትበል!»