1ነቢዩ ዕንባቆም የተቀበለው መልእክት፤
2«ያህዌ ሆይ፣ ለርዳታ ወደ አንተ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? «ግፍ በዛ!» በማለት ወደ አንተ ጮኽሁ፤ አንተ ግን አላዳንኸኝም፡፡
3ርኩሰትና በደልን ለምን እንዳይ አደረግኸኝ? ጥፋና ዐመፅ በፊቴ ናቸው፤ ፀብና ጭቅጭቅም እየበዛ ነው!
4ስለዚህ ሕግ ላልቶአል፤ ፍትሕ ተዛብቶአል፡፡ ክፉዎች ጻድቃንን ከብበዋል ስለዚህ ፍርድ ተጣሟል፡፡» ያህዌ እንዲህ በማለት ለዕንባቆም መለሰ
5«ቢነገራችሁ እንኳ የማታምኑትን አንድ ነገር በዘመናችሁ ስለማደርግ፣ ልብ አድርጋችሁ አሕዛብን እዩ፤ ተመልከቱ፤ እጅግም ተደነቁ፡፡
6ጨካኞቹንና ችኩሎቹን ከለዳውያንን ላስነሣ ነው፤ የራሳቸው ያልሆኑ ቤቶችን ለመውሰድ በምድሪቱ ስፋትና ርዝመት ይገሠግሣሉ፡፡
7እነርሱ አስፈሪና አስደንጋጭ ናቸው፤ ፍርዳቸውና ክብራቸው ከራሳቸው ይወጣል፡፡
8ፈረሶቻቸው ከነብር ይልቅ ፈጣኖች፣ ከማታም ተኩላ ይልቅ፣ አስፈሪዎች ናቸው፡፡ ፈረሶቻቸው በፍጥነት ይጋልባሉ፤ ነጥቆ ለመብላት እንደሚቸኩል ንስር ፈረሰኞቻቸው ከሩቅ ይመጣሉ፡፡
9ሁሉም ለዐመፅ ሥራ ይመጣሉ፤ ሰራዊታቸው እንደ ምድረ በዳ ነፋስ ይገሠግሣል፤ ምርኮኞችንም እንደ አሸዋ ይሰበስባል፡፡
10ነገሥታት ላይ ይሳለቃሉ፤ ገዥዎች ላይ ያፌዛሉ፡፡ በምሽጐች ላይ በመሳቅ ዐፈር ቆልለው ይይዟቸዋል፡፡
11ከዚያም እንደ ነፋስ አልፈው ይሄዳሉ፤ ጉልበታቸውን አምላካቸው ያደረጉ እነዚያን በደለኞች ይጠራርጋቸዋል፡፡ ዕንባቆም ለያህዌ ያቀረበው ሌላው ጥያቄ
12አንተ የእኔ አምላክ፣ የእኔ ቅዱስ፣ አንተ ከዘላለም ጀምሮ ያለህ አይደለህምን? እኛ አንሞትም፡፡ እንዲፈርዱ ያህዌ ሾሟቸዋል፤ አንተ ዐለት ሆይ፣ ይቀጡ ዘንድ ሥልጣን ሰጠሃቸው፡፡
13ዐይኖችህ እጅግ የነጹ በመሆናቸው ክፉ ነገርን መመልከት አይሆንላቸውም፤ አንተም ክፉ ነገር ሲሠራ ዝም ብለህ አታይም፤ ታዲያ፣ እነዚያን ዐመፀኞች ለምን ዝም ብለህ ትመለከታለህ? ዐመፀኛው ከራሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሰው ሲውጠውስ ለምን ዝም ትላለህ?
14ሰዎችን ባሕር ውስጥ እንዳለ ዓሣ፣ መሪ እንደሌላቸው በደረታቸው እየተሳቡ እንደሚሄዱ ፍጥረታት የምታደርጋቸው ለምንድነው?
15ዓሣ በመንጠቆ እንደሚያዝ ሁሉንም በመንጠቆ ይይዟቸዋል፤ ሰዎችን በመረቦቻቸው ይዘው ይሰበሰቧቸዋል፡፡ ደስ የሚሰኙትና ሐሤት የሚያደርጉት ከዚህ የተነሣ ነው፡፡
16የስቡ እንስሳት ድርሻዎቻቸው፣ የጣፈጠውም ሥጋ ምግባቸው ሆናልና ስለዚህ ለመረቦቻቸው ይሠዋሉ፤ ለአሸክላዎቻቸውም ያጥናሉ፡፡
17ታዲያ፣ መረቦቻቸውን ባዶ እያደረጉ፣ ያለ አንዳች ርኅራኄ ሕዝቦችን መግደል መቀጠል አለባቸውን?»