መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኦሪት ዘፍጥረት 9

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ኖኅንና ልጆቹን እንዲህ ሲል ባረካቸው፦ “ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት፤
2አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ በእንስሳት፣ በሰማይ ወፎች፣ በደረት በሚሳቡ ተንቀሳቃሽ ፍጡሮችና በባሕር ዓሦች፣ በምድር ላይ በሚገኙ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ላይ ይሁን። ሁሉም በሥልጣናችሁ ሥር ይሁኑ።
3ሕያውና ተንቀሳቃሽ ፍጡር ሁሉ ምግብ ይሁናችሁ፣ ለምለሙን ዕፅዋት እንደሰጠኋችሁ፣ አሁን ደግሞ ሁሉን ሰጠኋችሁ።
4ነገር ግን ሕይወቱ ማለት ደሙ ገና በውስጡ ያለበትን ሥጋ አትብሉ።
5ሰውን የገደለ ሁሉ ስለሟቹ ደም ተጠያቂ ነው፤ የሟቹን ሰው ደም ከገዳዩ ከእንስሳም ይሁን ከሰው እሻለሁ።
6የሰውን ደም የሚያፈስ ሁሉ ደሙ በሰው እጅ ይፈሳል፤ በእግዚአብሔር አምሳል እግዚአብሔር ሰውን ሠርቶታልና።
7እናንተ ግን ብዙ ተባዙ፣ ዘራችሁ በምድር ላይ ይብዛ ይንሠራፋም።”
8ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ለኖኅና ለልጆቹ እንዲህ አላቸው፦
9“እነሆ ከእናንተና ከእናንተ በኋላ ከሚመጣው ዘራችሁ ጋር ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤
10እንዲሁም ከእናንተ ጋር ከነበሩት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ከወፎች፣ ከእንስሳት ከእናንተ ጋር ከመርከቧ ከወጡት በምድር ላይ ካሉት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር ኪዳን እገባለሁ።
11ከእንግዲህ ሕይወት ያለው ፍጡር ሁሉ በጥፋት ውሃ እንደማይጠፋ፣ ዳግመኛም ምድርን የሚያጠፋ ውሃ ከቶ እንደማይመጣ ከእናንተ ጋር ኪዳን እገባለሁ።”
12እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፦ “በእኔና በእናንተ መካከል ከእናንተም ጋር ካሉ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ፣ ከሚመጣው ትውልድ ሁሉ ጋር፣ የማደርገው የኪዳኑ ምልክት ይህ ነው፤
13ቀስተ ደመናዬን በደመና ላይ አድርጋለሁ፤ ይህም በእኔና በምድር መካከል ለገባሁት ኪዳን ምልክት ይሆናል።
14ደመናን በምድር ላይ በጋረድሁና ቀስቴም በደመና ላይ በሚታይበት ጊዜ ሁሉ
15ከእናንተና ከሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር የገባሁትን ኪዳን አስባለሁ፤ ሕይወት ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ፣ ከእንግዲህ የጥፋት ውሃ ከቶ አይመጣም።
16ቀስቱ በደመና ላይ ተገልጦ በማይበት ጊዜ ሁሉ በእኔና በምድር ላይ ባሉ ሕያዋን ፍጡራን መካከል ያለውን ዘላለማዊ ኪዳን አስባለሁ።”
17ከዚያ በኋላም እግዚአብሔር ለኖኅ፦ “ይህ በእኔና በምድር ላይ በሚኖሩ ሕያዋን ሁሉ መካከል የገባሁት ኪዳን ምልክት ነው።” አለው።
18ከመርከቧ የወጡትም የኖኅ ልጆች ሴም፣ ካምና ያፌት ነበር፤ ካም የከነዓን አባት ነው።
19እነዚህ ሶስቱ የኖኅ ልጆች ሲሆኑ፣ በምድር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ የተገኙት ከነዚሁ ነው።
20ኖኅ ገበሬ መሆን ጀመረ፣ ወይንንም ተከለ።
21ከወይኑም ጠጅ ጠጥቶ ሰከረና በድንኳኑ ውስጥ እርቃኑን ተኛ።
22የከንዓን አባት ካም የአባቱን ዕርቃነ ሥጋ አየ፤ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው።
23ሴምና ያፌት ግን ልብስ ወስደው በትከሻቸው ላይ አደረጉና የአባታቸውን ዕርቃነ ሥጋ እንዳያዩ ፊታቸውን አዙረው የኋሊት በመሄድ የአባታቸውን ዕርቃነ ሥጋ ሸፈኑ።
24ኖኅ ከወይን ጠጁ ስካር ሲነቃ ታናሽ ልጁ ያደረገበትን አወቀ።
25ከዚህም የተነሣ፦ “ከነዓን የተረገመ ይሁን፤ ለወንድሞቹም አገልጋይ ይሁን።” አለ።
26ደግሞም፦ “የሴም አምላክ የሆነው እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፣ ከነዓንም የሴም አገልጋይ ይሁን።
27እግዚአብሔር የያፌትን ግዛት ያስፋ፤ ያፌት በሴም ድንኳኖች ይኑር፤ ከነዓን የያፌት አገልጋይ ይሁን።” አለ።
28ኖኅ ከጥፋት ውሃ በኋላ 350 ዓመት ኖረ።
29ኖኅ በአጠቃላይ 950 ዓመት ኖሮ ሞተ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።