መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኦሪት ዘፍጥረት 8

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እግዚአብሔር ኖኅንና ከእርሱ ጋር በመርከቧ ውስጥ የነበሩትን አራዊትና እንስሳት ሁሉ አሰበ። በምድር ላይ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ ውሃውም ጎደለ።
2የጥልቁ ምንጮችና የሰማይ መስኮቶች ተዘጉ፣ ዝናቡም መዝነቡን አቆመ።
3ውሃው ከምድር ላይ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጣ፤ ከመቶ ሃምሳ ቀን በኋላም የውሃው ከፍታ እጅግ ቀነሰ።
4በሰባተኛው ወር፤ በአሥራ ሰባተኛው ቀን መርከቧ በአራራት ተራሮች ላይ አረፈች።
5ውሃው እስከ አሥረኛው ወር ድረስ ቀስ በቀስ እየጎደለ ሄደ። በአሥረኛው ወር መጀመሪያው ቀን የተራሮች ጫፎች ታዩ።
6ከአርባ ቀን በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቧን መስኮት ከፍቶ፣
7ቁራን ወደ ውጭ ላከ፤ ቁራውም ውሃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር።
8ከዚያም በኋላ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ ገጽ ጎድሎ እንደሆነ ለማወቅ ርግብን ላከ፤
9ነገር ግን ውሃው ገና ምድርን ሁሉ ሸፍኖ ስለነበር ርግቢቱ የምታርፍበት ቦታ አላገኘችም፤ ስለዚህ ኖኅ ወዳለበት መርከብ ተመልሳ መጣች፤ ኖኅም እጁን ዘርግቶ ወደ መርከቡ ውስጥ አስገባት።
10ሰባት ቀን ከቆየ በኋላ ኖኅ ርግቧን እንደገና ላካት።
11እርሷም ወደ ማታ ተመለሰች፤ እነሆም የለመለመ የወይራ ቅጠል በአፏ ይዛ ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጉደሉን አወቀ።
12ደግሞም ሰባት ቀን ከቆየ በኋላ ኖኅ ርግቢቱን እንደገና አውጥቶ ላካት፤ በዚህ ጊዜ ግን ርግቢቱ ወደ እርሱ አልተመለሰችም።
13ኖኅ በተወለደ 601ኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ውሃው ከምድር ላይ ደረቀ። ኖኅ የመርከቡን ክዳን አንሥቶ ዙሪያውን ተመለከተ፣ ምድሪቱም እንደደረቀች አየ።
14በሁለተኛው ወር፣ በሃያ ሰባተኛው ቀን ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ደረቀች።
15ከዚያም እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው።
16“አንተና ሚስትህ፣ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ከመርከቧ ውጡ።
17እንዲዋለዱ፣ እንዲራቡና በምድር ላይ እንዲበዙ ከአንተ ጋር ያሉትን ወፎች፣ እንስሳትና በምድር ላይ የሚሳቡ ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ይዘሃቸው ውጣ።”
18ስለዚህ ኖኅ ከልጆቹ፣ ከሚስቱና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር ወጣ።
19እንስሳቱ ሁሉ፣ ወፎችም፣ በምድር የሚሳቡት፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ በየወገናቸው ከመርከቧ ወጡ።
20ኖኅም ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ። ንፁሕ ከሆኑት እንስሳትና ንፁሕ ከሆኑት ወፎች አንዳንዶቹን ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።
21እግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን መዓዛ አሸተተ፣ በልቡም እንዲህ አለ፦ “ምንም እንኳ ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ ቢሆንም በእርሱ ምክንያት ሁለተኛ ምድርን አልረግማትም፤ አሁን እንዳደረግሁት ሕያዋን ፍጡራንን ዳግመኛ አላጠፋም።
22ምድር እስካለች ድረስ የዘር ወቅትና መከር፣ ሙቀትና ቅዝቃዜ፣ በጋና ክረምት፣ ቀንና ሌሊት አይቋረጡም።”
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።