1እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፦ “በዚህ ትውልድ መካከል አንተን ጻድቅ ሆነህ አግኝቼሃለሁና ቤተሰብህን በሙሉ ይዘህ ወደ መርከቧ ግባ።
2ከንፁህ እንስሳት ሁሉ ሰባት ሰባት ወንድና ሴት፣ ንፁሕ ካልሆኑት እንስሳት ደግሞ ሁለት ሁለት ወንድና ሴት ከአንተ ጋር አስገባ።
3እንዲሁም ከሰማይ ወፎች ወገን ሰባት ወንዶችና ሰባት ሴቶች በምድር ላይ ለዘር እንዲተርፉ ከአንተ ጋር ታስገባለህ።
4ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በመድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁ፤ የፈጠርሁትንም ሕያው ፍጡር ሁሉ ከምድር ላይ አጠፋለሁ።”
5ኖኅም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።
6የጥፋት ውሃ በምድር ላይ በወረደ ጊዜ ኖኅ የ600 ዓመት ሰው ነበር።
7ኖኅና ወንዶች ልጆቹ ሚስቱና የልጆቹ ሚስቶች ከጥፋት ውሃ ለማምለጥ ወደ መርከቡ ገቡ።
8ንፁሕ ከሆኑትና ንፁሕ ካልሆኑት እንስሳት ከወፎችና በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጡራን ሁሉ
9ጥንድ ጥንድ ወንድና ሴት ሆነው ወደ ኖኅ መጡ፤ እግዚአብሄር ኖኅን ባዘዘው መሠረትም ወደ መርከቧ ገቡ።
10ከሰባት ቀንም በኋላ የጠፋት ውሃ በምድር ላይ መጣ።
11ኖኅ በተወለደ በ600ኛው ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ቀን የታላቁ ጥልቅ ምንጮች በሙሉ ተነደሉ፤ የሰማይ መስኮቶችም ተከፈቱ።
12ዝናቡም መዝነብ ጀመረ፣ አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ባለማቋረጥ በምድር ላይ ዘነበ።
13ዝናቡ መዝነብ በጀመረበት ቀን ኖኅና ሚስቱ ከልጆቻቸው ጋር ከሴም ከካም ከያፌትና ከሶስቱም ልጆቻቸው ሚስቶች ጋር ወደ መርከቡ ገቡ።
14ከአራዊት ከእንስሳት በደረታቸው እየተሳቡ ከሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችና በሰማይ ከሚበሩ ወፎች ከእያንዳንዱ ዓይነት አብረዋቸው ገቡ።
15የሕይወት እስትንፋስ ያለባቸው ፍጡራን በሙሉ ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ከኖኅ ጋር ወደ መርከቡ ገቡ።
16ከሕያዋንም ፍጡራን ሁሉ እግዚአብሔር ኖኅን ባዘዘው መሠረት ወንድና ሴት እየሆኑ ገቡ፤ ከዚያም እግዚአብሔር የመርከቡን በር ከውጭ ዘጋ።
17የጥፋት ውሃም ለአርባ ቀናት ያለመቋረጥ በምድር ላይ ዘነበ ውሃው እየጨመረ በሄድ መጠን መርከቧን ከምድር ወደ ላይ አነሳት።
18ውሃው በምድር ላይ በጣም እየጨመረና ከፍ እያለ ሲሄድ፣ መርከቧ በውሃ ላይ ተንሳፈፈች።
19ውሃው በጣም ከፍ በማለቱ፣ ከሰማይ በታች ያሉትን ታላላቅ ተራሮች ሁሉ ሸፈናቸው።
20ውሃው ከተራሮች ጫፍ በላይ 7ሜትር ያህል ከፍ አለ።
21በምድር ላይ የነበሩ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ፦ ወፎች፣ የቤት እንስሳት፣ አራዊት፣ በምድር የሚርመሰመሱ ፍጡራን ሰዎችም በሙሉ ጠፉ።
22የሕይወት እስትንፋስ ያላቸው በምድር የነበሩ ፍጡራን ሁሉ ሞቱ።
23ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ሁሉ ከሰዎች ጀምሮ እንስሳት፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራንና የሰማይ ወፎች ሁሉም ከምድር ገጽ ጠፉ። ኖኅና ከእርሱ ጋር በመርከቧ ውስጥ የነበሩት ብቻ ተረፉ።
24ውሃውም ምድርን ሸፍኖ መቶ አምሳ ቀን ቆየ።