1የሰው ልጆች በምድር ላይ እየበዙ ሲሄዱ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው።
2የእግዚአብሔር ልጆችም የሰዎች ሴቶች ልጆች የሚስብ ውበት እንዳላቸው ተመለከቱ። ከእነርሱ መካከልም የመረጧቸውን ሚስቶች አድርገው ወሰዱ።
3እግዚአብሔርም፦ “እርሱ ሥጋ ስለሆነ መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፤ ዕድሜውም 120 ዓመት ይሆናል” አለ።
4የእግዚአብሔር ልጆች ከሰዎች ሴቶች ልጆች ጋብቻ በፈጸሙና ልጆችን በወለዱበት በዚያን ጊዜ ከዚያም በኋላ ኔፊሊም የተባሉ ግዙፍ ሰዎች በምድር ላይ ነበሩ። እነርሱም በጥንት ዘመን ዝናን ያተረፉ ኅያላን ነበሩ።
5እግዚአብሔር የሰው ልጆች ክፋት በምድር ላይ እየበዛ እንደሆነና የልቡም ሃሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ።
6እግዚአብሔር የሰው ልጆችን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ ልቡም አዘነ።
7በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር፦ “የፈጠርሁትን የሰው ልጅ ከምድር ገጽ አጠፋለሁ፤ ስለፈጠርኋቸው ተጸጽቻለሁና ከእነርሱም ጋር እንስሳትን፣ በደረታቸው የሚሳቡትን ፍጥረታትና የሰማይ ወፎችን ሁሉ አጠፋለሁ” አለ።
8ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አገኘ።
9የኖኅ ታሪክ እንደሚከተለው ነው። ኖኅ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ጻድቅና ከበደል የራቀ ሰው ነበር፤ የእግዚአብሔርንም መንገድ የሚከተል ሰው ነበር።
10ኖኅ ሴም፣ ካምና ያፌት የተባሉትን ሶስት ወንዶች ልጆች ወለደ።
11በእግዚአብሔር ፊት በክፉ ሥራ ረከሰች በዓመፅም ተሞላች።
12እግዚአብሔር ምድርን ተመለከተ፣ የተበላሸች እንደሆነችና በምድር የሚኖሩትም ሰዎች ሁሉ በክፋት እንደሚኖሩ አየ።
13እግዚአብሔርም ኖኅን፦ “ሥጋን የለበሰ ሁሉ ፍጻሜ ደርሶአል፣ ከእነርሱ የተነሳ ምድር በግፍ ተሞልታለችና። እኔም በእርግጥ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ።
14አንተ ግን ከጥሩ እንጨት መርከብ ሥራ፤ መርከቧም ክፍሎች እንዲኖራት አድርግ፤ ውስጧንና ውጭዋንም በቅጥራን ለቅልቀው።
15እንደዚህ አድርገህ ሥራት፦ ርዝመቷ 140 ሜትር፣ ወርዷ 23 ሜትር፣ ከፍታዋ 13. 5 ሜትር ይሁን።
16ለመርከቧ ጣራ አብጅላት፣ ጣራና ግድግዳው በሚጋጠምበት ቦታ ግማሽ ሜትር ክፍተት ተው፤ ከጎኗ በር አውጣላት፤ ባለ ሦስት ፎቅ አድርገህ ሥራት።
17እኔም ከሰማይ በታች የሕይወት እስትንፋስ ያለባችውን ፍጡራን ሁሉ ለማጥፋት እነሆ በምድር ላይ የጥፋት ውሃ አወርዳለሁ፤ በምድር ላይ ያለ ሁሉ ይጠፋል።
18ከአንተ ጋር ግን ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ አንተና ሚስትህ፣ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ከአንተ ጋር ወደ መርከቧ ትገባላችሁ።
19ከአንተ ጋር በሕይወት እንዲቆዩ ከሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ወንድና ሴት እያደረግህ ሁለት ሁለቱን ወደ መርከቧ ታስገባለህ።
20ከእያንዳንዱ የወፍ ወገን፣ ከእያንዳንዱ የእንስሳ ወገን፣ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረት ሁሉ በየወገናቸው በሕይወት ይቆዩ ዘንድ ወደ አንተ ይምጡ።
21ለአንተና ለእነዚህ ፍጥረቶች ሁሉ የሚበቃ ልዩ ልዩ ዓይነት ምግብ በመርከቡ ውስጥ አከማች።”
22ኖኅም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።