1ከጥቂት ጊዜ በኋላም፣ “አባትህ ታሞአል” ተብሎ ለዮሴፍ ስለተነገረው ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ሄደ።
2ለያዕቆብ፣ “ልጅህ ዮሴፍ ወደ አንተ መጥቶአል” ተብሎ በተነገረው ጊዜ፣ እስራኤል ተበረታትቶ አልጋው ላይ ተቀመጠ።
3ያዕቆብም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ሁሉን የሚችል አምላክ በከነዓን ምድር ሎዛ በምትባል ቦታ ተገለጠልኝ፤ ባረከኝም፤
4እንዲህም አለኝ፤ ‘ፍሬያማ አደርግሃለሁ፣ ዝርያዎችህም ብዙ ሕዝቦች ይሆናሉ፣ ይህችንም ምድር ለዝርያዎችህ ለዘላለም ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ’ አለኝ።”
5ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት በግብፅ የወለድሃቸው ሁለቱ ልጆችህ ከእንግዲህ የእኔ ልጆች ሆነው ይቆጠራሉ፤ ሮቤልና ስምዖን ልጆቼ እንደሆኑ ሁሉ፣ ኤፍሬምና ምናሴም ልጆቼ ይሆናሉ።
6ከእነርሱ በኋላ የሚወለዱልህ ልጆች ግን፣ የአንተ ይሁኑ፤ በርስት ድልድላችው ግን በወንድሞቻቸው ስም ይቆጠራሉ።
7ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ስመለስ ኤፍራታ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረኝ፤ እናትህ ራሔል በከነዓን ምድር ሞታብኝ አዘንሁ። እኔም ወደ ኤፍራታ ማለት ወደ ቤተ ልሔም በሚወስደው መንገድ ዳር ቀበርኋት።”
8እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች ባየ ጊዜ፣ “እነዚህ እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀ፤
9ዮሴፍም፣ “እነዚህ እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ናቸው” ብሎ መለሰለት፤ እስራኤልም “አቅርባቸውና ልመርቃቸው” አለ።
10በዚህ ጊዜ እስራኤል ዓይኖቹ በእርጅና ምክንያት በመድከማቸው አጥርቶ ማየት ይሳነው ነበር፤ ስለዚህ ዮሴፍ ልጆቹን አባቱ ዘንድ አቀረባቸው፤ አባቱም ስሞ አቀፋቸው።
11እስራኤልም ዮሴፍን፣ “ዓይንህን እንደገና ዐያለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ልጆችህን ጭምር ለማየት አበቃኝ” አለው።
12ዮሴፍም ልጆቹን ከእስራኤል ጉልበት ፈቀቅ በማድረግ አጎንብሶ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ።
13ከዚያም ዮሴፍ ሁለቱን ልጆቹን ይዞ ኤፍሬምን ከራሱ በስተቀኝ ከእስራኤል በስተግራ፣ ምናሴን ደግሞ ከራሱ በስተግራ ከእስራኤል በስተቀኝ በኩል አቀረባቸው።
14እስራኤል ግን ቀኝ እጁን በታናሹ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረ፣ ግራ እጁንም በቀኝ እጁ ላይ አስተላልፎ በበኩሩ በምናሴ ላይ አኖረ።
15ከዚህ በኋላ ዮሴፍን ባረከ፤ እንዲህም አለው፤ “አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ መንገዱን በመከተል ያገለገሉትና ለእኔም እስከ ዛሬ ድረስ በዘመኔ ሁሉ እረኛ የሆነኝ አምላክ፣
16ከጉዳትም ሁሉ የታደገኝ ምልአክ፣ እርሱ እነዚህን ልጆች ይባርክ፤ እነርሱም በስሜ፣ በአባቶቼ በአብርሃምና በይስሐቅ ስም ይጠሩ፣ በምድር ላይ እጅግ ይብዙ።
17ዮሴፍ አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ማድረጉን ሲያይ ቅር ተሰኘ፤ ከኤፍሬም ራስ ላይ አንስቶ በምናሴ ራስ ላይ ለማኖር የአባቱን እጅ ያዘ፤
18ዮሴፍም፣ “አባቴ ሆይ፣ እንዲህ አይደለም በኩሩ ይህኛው ስለሆነ፣ ቀኝ እጅህን እርሱ ራስ ላይ አድርግ” አለው።
19አባቱ ግን፣ “ዐውቃለሁ፣ ልጄ ዐውቃለሁ፣ እርሱም እኮ ሕዝብ ይሆናል፤ ታላቅም ይሆናል፤ ይሁን እንጂ፣ ታናሽ ወንድሙ ከእርሱ ይበልጣል፤ ዘሮቹም ታላቅ ሕዝቦች ይሆናሉ” ብሎ እምቢ አለው።
20በዚያን ዕለት ባረካቸው፣ እንዲህም አላቸው፤ “እስራኤላውያን በሚመርቁበት ጊዜ የእናንተን ስም በማስታወስ፤ ‘እግዚአብሔር እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርጋችሁ’ ይላሉ” በዚህ ሁኔታም ኤፍሬምን ከምናሴ አስቀደመው።
21ከዚህ በኋላ እስራኤል ዮሴፍን እንዲህ አለው፣ እኔ የምሞትበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ወደ አባቶቻችሁም ምድር መልሶ ያገባችኋል።
22እነሆ በሰይፌና በቀስቴ ከአሞራውያን እጅ የወሰድኋትን ምድር ከወንድሞችህ ድርሻ አብልጬ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ።”