1ዮሴፍም ወደ ፈርዖን ሄዶ፣ “አባቴና ወንድሞቼ በጎቻቸውን፣ ፍየሎቻቸውን እንዲሁም ያላቸውን ሁሉ ይዘው ከከነዓን አገር መጥተው በጌሤም ሰፍረዋል” አለው።
2ከወንድሞቹም መካከል አምስቱን መርጦ፣ ፈርዖን ፊት አቀረባቸው።
3ፈርዖን የዮሴፍን ወንድሞች፣ “ሥራችሁን ምንድነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም ፈርዖንን፣ “እኛ አገልጋዮችህ ልክ እንደአባቶቻችን ከብት አርቢዎች ነን” አሉት።
4ደግሞም፣ “በከነዓን ምድር ራቡ እጅግ የጸና በመሆኑ በጎችና ፍየሎች የሚሰማሩበት በማጣታቸው፣ ለጊዜው እዚህ ለመኖር መጥተናል፤ አሁንም ባሮችህ በጌሤም ምድር እንድንኖር እንድትፈቅድልን እንለምንሃለን” አሉት።
5ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “አባትንህና ወንድሞችህ ወደ አንተ መጥተዋል፤
6የግብፅ ምድር እንደሆነ በእጅህ ነው፤ አባትህንና ወንድሞችህን ምርጥ በሆነው ምድር አስፍራቸው፤ በጌሤም ይኑሩ። ከመካከላቸው ልዩ ችሎታ ያላቸው መኖራቸውን የምታውቅ ከሆነ፣ የከብቶቼ ኅላፊዎች አድርጋቸው።”
7ከዚህ በኋላ ዮሴፍ አባቱን ያዕቆብን ቤተ መንግሥት አግብቶ በፈርዖን ፊት አቀረበው፤ ያዕቆብ ፈርዖንን ከመረቀው በኋላ
8ፈርዖን፣ “ለመሆኑ ዕድሜህ ምን ያህል ነው?” ሲል ያዕቆብን ጠየቀው።
9ያዕቆብም ለፈርዖን፣ “በምድር ላይ በእንግድነት ያሳለፍሁት ዘመን 130 ዓመት ነው፤ ይህም አባቶቼ በእንግድነት ከኖሩበት ዘመን ጋር ሲነጻጸር አጭር ነው፤ ችግር የበዛበትም ነበር” ሲል መለሰለት።
10ከዚያም ያዕቆብ ፈርዖንን መርቆ፣ ተሰናብቶት ወጣ።
11ዮሴፍም አባቱንና ወንድሞቹን በግብፅ እንዲኖሩ አደረገ፤ ፈርዖን በሰጠውም ትእዛዝ መሠረት ምርጥ ከሆነው ምድር ራምሴን በርስትነት ሰጣቸው።
12ዮሴፍም ለአባቱ፣ ለወንድሞቹና ለመላው የአባቱ ቤተ ሰዎች በልጆቻቸው ቁጥር ልክ ቀለብ እንዲሰፈርላቸው አደረገ።
13በመላው ምድር እህል ባለመኖሩ ራቡ እየጸና ሄደ፤ ከዚህ የተነሣም ግብፅና ከነዓን በራብ እጅግ ተጎዱ፤
14ዮሴፍ የግብፅና የከነዓን ሰዎች እህል በመሸመት የከፈሉትን ገንዘብ ሁሉ ሰብስቦ ወደ ፈርዖን ቤተ መንግሥት አስገባ።
15የግብፅና የከነዓን ሕዝቦችም ገንዘባቸው ባለቀ ጊዜ፣ ግብፃውያን ሁሉ ወደ ዮሴፍ ቀርበው፣ “የምንበላው እህል ስጠን፣ ገንዘባችን አልቆብናል፤ ዓይንህ እያየ እንዴት በራብ እንለቅ?” አሉት።
16ዮሴፍም ከብቶቻችሁን አምጡ፣ ገንዘባችሁ ካለቀ በከብቶቻችህ ለውጥ እህል እሰጣችኋለሁ አለ።
17ስለዚህ ከብቶቻቸውን ወደ ዮሴፍ አምጡ፤ እርሱም በፈረሶቻቸው፣ በበጎቻቸው፣ በፍየሎቻቸው፣ በከብቶቻቸውና በአህዮቻቸው ለውጥ እህል ሰጣቸው። በከብቶቻቸው ልዋጭ ባገኙት ምግብ በዚያ ዓመት ሳይራቡ እንዲያልፉ አደረጋቸው።
18ያም ዓመት ካለፈ በኋላ ሕዝቡ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ዮሴፍ መጥተው እንዲህ አሉት፣ “እንግዲህ ከጌታችን የምንሰውረው ምንም ነገር የለም፤ ገንዘባችን አልቆአል፤ ከብቶቻችንንም አስረክበንሃል፤ እንግዲህ ለጌታችን የምንሰጠው፣ ከሰውነታችንና ከመሬታችን በቀር ሌላ ምንም ነገር የለንም።
19ታዲያ እያየኸን እንዴት እንለቅ? መሬታችንም ለምን ጠፍ ሆኖ ይቅር? እኛንና መሬታችንን ውሰድና በለውጡ እህል ስጠን፤ እኛ የፈርዓን አገልጋዮች እንሆናለን፤ መሬታችንም የእርሱ ይሁን፣ እኛም እንዳንሞት መሬታችንም ጠፍ ሆኖ እንዳይቀር የምንዘራው ዘር ስጠን።
20ስለዚህ ዮሴፍ የግብፅን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛለት፤ ራቡም እጅግ ስለጸናባቸው ግብፃውያን ሁሉ መሬታቸውን ሸጡ፣ ምድሪቱም የፈርዖን ርስት ሆነች።
21ዮሴፍ በግብፅ አገር ዳር እስከ ዳር ያሉት ሰዎች ሁሉ የንጉሡ አገልጋዮች እንዲሆኑ አደረገ።
22ሆኖም ዮሴፍ የካህናቱን መሬት አልገዛም፤ ምክንያቱም ካህናቱ ከፈርዖን ቋሚ አበል ስለሚያገኙ እርሱም ከሚሰጣቸው አበል ምግብ ያገኙ ስለነበረ መሬታቸውን አልሸጡም።
23ዮሴፍ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፣ “እነሆ፣ ዛሬ እናንተንም መሬታችሁንም ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁና ይህን ዘር ወስዳችሁ በመሬት ላይ ዝሩ።
24መከሩ በሚሰበሰብበት ጊዜ ግን ከአምስት እጅ አንዱን ለፈርዖን ታስገባላችሁ፣ ከአምስት እጅ አራቱን ደግሞ ለመሬታችሁ ዘር፣ እንዲሁም ለራሳችሁ፣ ለቤተ ሰቦቻችሁና ለልጆቻችሁ ምግብ ታደርጉታላችሁ።”
25እነርሱም፣ “እንግዲህ ሕይወታችንን አትርፈህልናል፤ በጌታችን ፊት ሞገስ ካገኘን ለፈርዖን ገባሮች እንሆናለን” አሉት።
26ስለዚህ ዮሴፍ የምርቱ አንድ አምስተኛ ለፈርዖን እንዲገባ የሚያዝ የመሬት ሕግ አወጣ፤ ይህም ሕግ እስከ ዛሬ ይሠራበታል። በፈርዖን እጅ ያልገባው መሬት የካህናቱ ብቻ ነው።
27በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን በግብፅ አገር በጌሤም ይኖሩ ነበር፣ በዚያም ሀብት ንብረት አፈሩ፤ ቁጥራቸውም እጅግ እየበዛ ይሄድ ጀመር።
28ያዕቆብ በግብፅ ዐሥራ ሰባት ዓመት ኖረ፣ ዕድሜውም አንድ መቶ አርባ ሰባት ዓመት ነበር።
29እስራኤልም የሚሞትበት ጊዜ መቃረቡን እንደተረዳ ልጁን ዮሴፍን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “በአንተ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ እጅህን በጭኔ ላይ አኑረህ፣ በጎነትንና ታማኝነትን ልታደርግልኝ ቃል ግባልኝ፤ በምሞትበት ጊዜ በግብፅ አትቅበረኝ፤
30እኔም ከአባቶቼ ጋር ሳንቀላፋ ከግብፅ አውጥተህ እነርሱ በተቀበሩበት ቦት ቅበረኝ” ዮሴፍም፣ “እሺ፣ እንዳልኸኝ አደርጋለሁ” አለ።
31ያዕቆብ፤ “በል ማልልኝ” አለው። ዮሴፍም ማለለት፣ እስራኤልም በአልጋው ራስጌ ላይ ሆኖ ጎንበስ አለ።