መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኦሪት ዘፍጥረት 49

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ያዕቆብ ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በአንድነት ተሰብሰቡና ወደፊት የሚገጥማችሁን ነገር ልንገራችሁ፣
2እናንተ የያዕቆብ ልጆች፣ በአንድነት ተሰብስባችሁ ስሙ፣ አባታችሁ እስራኤል የሚነግራችሁንም አድምጡ።
3ሮቤል፣ ኃይልና የጎልማሳነት ብርታት በነበረኝ ጊዜ የወለድሁህ የበኩር ልጄ ነህ። ከልጆቼ ሁሉ በክብርና በኃይል የምትበልጥ አንተ ነህ።
4ይሁን እንጂ እንደ ውሃ የምትዋልል ስለሆንህ የበላይ አለቅነት ለአንተ አይገባም፣ ምክያንቱም የአባትህን መኝታ ደፍረሃል ምንጣፌንም አርክሰሃል።
5“ስምዖንና ሌዊ ወንድማማቾች ናቸው፣ ዓመፅ ለመፈጸም የጦር መሣሪያዎቻቸውን ያነሳሉ።
6ወደ ሸንጎአቸው አልግባ፣ ጉባኤያቸው ውስጥ አልገኝ፣ በቁጣ ተነሣስተው ወንዶችን ገድለዋል፣ የበሬዎችንም ቋንጃ እንደፈለጉ ቆራርጠዋል።
7እጅግ አስፈሪ የሆነ ቁጣቸው፣ ጭከና የተሞላ ንዴታቸው የተረገመ ይሁን፤ በያዕቆብ እበትናቸዋለሁ፣ በመላው እስራኤልም አሠራጫቸዋለሁ።
8ይሁዳ ወንድሞችህ ያመሰግኑሃል፣ እጅህም የጠላቶችህን አንገት አንቆ ይይዛል፣ የአባትህ ልጆች በፊትህ ተደፍተው ይስግዱልሃል።
9ይሁዳ እንደ ደቦል አንበሳ ነው፣ ከዐደንህ የምትመለስ ልጄ፣ እንደ አንበሳ ያደፍጣል በምድርም ላይ ይተኛል፤ እንደ እንስት እንበሳም ያደባል፣ ታዲያ ማን ሊቀሰቅሰው ይደፍራል?
10በትረ መንግስሥት ከይሁዳ እጅ አይወጣም፤ የገዥነት ምርኩዝም ከእግሮቹ መካከል፣ ሕዝቦች ሁሉ የሚታዘዙለት ‘ሴሎ’ እስኪመጣ ድረስ፣ ሕዝቦች ሁሉ ይታዘዙለታል።
11አህያውን በወይን ግንድ፣ ውርንጫውንም በምርጡ የወይን ሐረግ ቅርንጫፍ ላይ ያስራል፣ ልብሱን በወይን ጠጅ፣ መጎናጸፊያውንም በወይን ጭማቂ ያጥባል።
12ዓይኖቹ ከወይን ጠጅ የቀሉ፣ ጥርሶቹም ከወተት ይልቅ የነጡ ይሆናሉ።
13ዛብሎን በባሕር ዳርቻ ይኖራል፣ የመርከቦቹ መጠጊያም ይሆናል፣ ወሰኑም እስከ ሲዶና ይደርሳል።
14ይሳኮር፣ አጥንተ ብርቱ አህያ በጭነት መካከል የሚተኛ፣ ማረፊያ ቦታው መልካም፣
15ምድሪቱም አስደሳች መሆኗን ሲያይ፣ ትከሻውን ለሸክም ዝቅ ያደርጋል ከባድ የጉልበት ሥራም ይሠራል።
16ዳን ከእስራኤል ነገዶች እንደ አንዱ ሆኖ በራሱ ሕዝብ ላይ ይፈርዳል።
17ዳን የመንገድ ዳር እባብ፣ የመተላለፊያም መንገድ እፉኝት ነው፤ ጋላቢው የኋሊት እንዲወድቅ፣ የፈረሱን ሰኮና ይነክሳል።
18እግዚአብሔር ሆይ፣ ማዳንህን እጠባበቃለሁ።
19ጋድን ወራሪዎች አደጋ ይጥሉበታል፣ እርሱ ግን ዱካቸውን ተከታትሎ ብድሩን ይመልሳል።
20አሴር ማዕደ ሰፊ ይሆናል፤ ለነገሥታትም የሚስማማ ምግብ ያቀርባል።
21ነጻ እንደተለቀቀች ሚዳቋ ነው፣ የሚያማምሩ ግልገሎች ይኖሩታል።
22ዮሴፍ፤ ፍሬያማ የወይን ተክል፣ በምንጭ ዳር የተተከለ ወይን ነው። ሐረጎቹ ቅጥርን ያለብሳሉ።
23ቀስተኞች በብርቱ ያጠቁታል፤ በቀስታቸውም እየነደፉ ያሳድዱታል፤
24ነገር ግን በያዕቆብ ኃያል አምላክ ክንድ፣ እረኛም በሆነው በእስራኤል አለት ቀስቱ ጸና ጠንካራ ክንዱም ቀልጣፋ ሆነ።
25አንተን በሚረዳህ በአባትህ አምላክ፣ በሚባርክህ ሁሉን በሚችል አምላክ፣ ከላይ ከሰማይ በሚገኝ ረድኤት፣ ከምድር ጥልቅ በሚገኝ በረከት፣ ከማኅፀንና ከጡት በሚገኝ ምርቃት ይባርክሃል።
26ከጥንት ተራሮች በረከት፣ ከዘላለም ኮረብቶች ምርቃት ይልቅ፣ የአባትይ በረከት ይበልጣል፤ ይህ ሁሉ በዮሴፍ ራስ ላይ ይውረድ፤ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነውም ግንባር ላይ ይረፍ።
27ብንያም ነጣቂ ተኩላ ነው፤ ያደነውን ማለዳ ይበላል፤ የማረከውን ማታ ያከፋፍላል።
28እነዚህ ሁሉ ዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ናቸው። ይህም እያንዳንዳቸውን ተገቢ በሆነው በረከት አባታቸው ሲባርካቸው የተናገረው ቃል ነው።
29ከዚህ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “እኔ የምሞትበትና ወደ ወገኖቼ የምሰበሰብበት ጊዜ ደርሶአል፤ ስለዚህ በኬጢያዊው በኤፍሮን እርሻ ውስጥ ባለችው ዋሻ ከአባቶቼ ዘንድ ቅበሩኝ፤
30ይህንን በከነዓን ምድር በመምሬ አጠገብ በማክፌል እርሻ ውስጥ ያለውን ዋሻ የመቃብር ቦታ እንዲሆን ከኬጢያዊው ኤፍሮን ላይ የገዛው አብርሃም ነው።
31በዚያ አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ተቀብረዋል፤ በዚያ ይስሐቅና ሚስቱ ርብቃ ተቀብረዋል፤ እኔም ልያን የቀበርኋት እዚያው ነው፤
32እርሻውና ዋሻው የተገዙት ከኬጢያውያን ላይ ነው።”
33ያዕቆብ እነዚህን ቃላት ለልጆቹ ተናግሮ እንዳበቃ እግሮቹን በአልጋው ላይ ሰብስቦ የመጨረሻ ትንፋሹን ተንፍሶ ሞተ፣ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።